የአማራን መጨፍጨፍ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ሊያወግዘውና ሊያስቆመው ይገባል!!
ኢትዮጵያ ሀገራችን ታፍራና ተከብራ በነጻነት ጸንታ የኖረች ሀገር ናት ውድ ልጆቿ በጀግንነት በብዙ አውደግንባር ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ክስክሰው ተጠብቃ እንድትኖር አድርገዋታል ብዙ መሪዎችም ሀገራችንን በልዩ ፍቅር መርተዋታል፤ በንግሥናቸው ዘመን ብዙ ተግዳሮት ቢገጥማቸውም የሕዝባቸውን አንድነት ለመጠበቅና ሃገራችን በዓለም ሕዝብ ፊት ከምትታይበት የክብር ማማ እንዳትወርድ ሕዝቦቿም በማንም ፊት እንዳይናቁ ትውልድ የማይረሳውን ታሪክ ሰርተው በፍጹም ቁርጠኝነት ብዙ ተጋድሎ በመፈጸም የኢትዮጵያን ሉዑላዊነት በክብር ጠብቀው ለትውልድ አስረክበዋል። ዛሬ ግን ታሪክ ተቀይሮ የኢትዮጵያውያን ደም በየቦታው እንደ ጎርፍ ፈሷል፣እጅግ በሚዘገንን አሰቃቂ ግድያ ሕዝቧቿ በገዛ ቀያቸው በየቦታው የግፍ ሞት ሞተዋል፣ ህጻናት ታርደዋል፣ አረጋውያን በገጀራ ተጨፍጭፈዋል፣ሴቶች በባሎቻቸው ፊት ተደፍረው ተገድለዋል፣ወጣቶች በጥይት ረግፈዋል፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ከክልሌ ውጣ በሚሉ ጽንፈኛ ብሔርተኞች ሐብትና ንብረታቸውን ተዘርፈው፣ ለዘመናት ከኖሩበትና ተወልደው ካደጉበትና ተድረው ለወግ ማዕረግ ከበቁበት ምድር በግፍ ተፈናቅለው መድረሻ አጥተው በየሜዳው ወድቀዋል።ይህ ሁሉ ግፍና አሰቃቂ በደል ሦስት ዓመት ሙሉ ያለማቋረጥ በሕዝብ ላይ ሲፈጸም የኢትዮጵያ መንግሥት ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ የዜጎችን ሕልውናና ደህንነት የመታደግ ተቀዳሚ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት አልቻለም።
በቅርቡ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣዬ፣ በአንጾኪያ ወረዳ ስር ባሉ ካራቆሬ፣ ቆሪሜዳ፣ ማጀቴ፣ መስኖ ካብሰራምባ፣ ገተም ውሃ፣ ኩሪብሪ፣ ዋጮ እና ዘንቦ ቀበሌዎች እና በቀወት ወረዳ ደግሞ ዙጢ ተብሎ ከሚጠራው የከተማው (ሸዋሮቢት) ቀበሌ ወጣ ብለው በሚገኙት የጅሌ ጥሙጋ አጎራባች አካባቢዎች በተለይም በባልጪ፣ በጀውሃ፣ ኩሪብሪ፣ በነጌሶ እና ሌሎች አካባቢዎች በተለይ በአጣዬና አካባቢው ሚያዝያ 6 ቀን 2013 በነዋሪዎች ላይ ተኩስ ተከፍቶ በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ በዳቦ ስሙ ኦነግ ሼኔ ተብሎ የሚጠራውና በኦሮምያ ባለሥልጣናት የሚደገፈው ገዳይና አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ባለፉት ረጅም ዘመናት ተከስቶ የማያውቅ ክቡር የሰው ልጅን ህይወት እንደ እንሰሳ ያረደበት፣ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ያወደመበት፣ አብያተክርስቲያናትን ያቃጠለበት በመሆኑ ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በዜጎች ላይ ለደረሰው እልቂት፤ ሰቆቃና መፈናቀል የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ መንግሥት በአሸባሪዎቹ ላይ አፋጣኝና የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ለተጎጂዎችም ተገቢው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና መልሶ የማቋቋም ጠንካራ ድጋፍ እንዲሰጥ አጥብቆ ያሳስባል።
በተመሳሳይ አደጋ ከሦስት ሳምንታት በፊት በዚሁ አካባቢ ከመጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም የበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት መቀጠፉ ይታወቃል ። በግጭቱ የደረሰው ጉዳት በዝርዝር ባይታወቅም፤ በአካባቢው ነዋሪዎች እንደተገለጸውና እንዲሁም የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋምን ጠቅሶ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ከ300 በላይ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
ጉዳዩን አሳሳቢና ውስብስብ የሚያደርገው ይህ አጥፊ ቡድን ይህንን የሽብር ወንጀልና አደጋ ከማድረሱ 24 ሰአት በፊት ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓም ከሌሊቱ 11 ሰአት ላይ ከአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት የመጣ ትእዛዝ በሚል የአማራ ልዩ ሀይልን ከአጣዪ፣ ከሸዋሮቢት፣ ከማጀቴ እና ከጀቡሀ በፍጥነት ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ ለአምስት ቀን ተልእኮ ግዳጅ በመስጠት ከነሙሉ ትጥቁ እንዲነሳ ከተደረገ በኋላ ሰራዊቱ በተነሳ በ24 ሰአት ውስጥ የሽብር መጣንባችሁ የሚል መልእክት በማሰራጨት ሚያዝያ 6 ቀን 2013 የጥፋት ዘመቻውና ጭፍጨፋው ተፈፅሟል።
ማጀቴ ከተማ ላይ በአንድ ግለሰብ ሞት እና የንብረት ውድመት የተጀመረው ጭፍጨፋ በስፋት ቀጥሎ ከፍተኛ የታጠቀ ኃይል ወደ አካባቢው በመግባት በአጣዬ፣ በካራቆሬ፣ በአንጾኪያና በኤፍራታ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል የተፈጸመው ጥቃትም አደገኛና ዘግናኝ ነው በጥቃቱ የንጹሃን ሰዎች ሕይወት አልፏል ከፍተኛ የሆነ ንብረትም ወድሟል።
በእነዚህ አምስት ቀናት ውስጥ በደረሰው ጥቃት ከሩብ ሚሊዮን (250,000) ዜጎች በላይ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በመንዝ ሞላሌ፤ በደብረሲና ከተማ እና በኮምቦልቻ ተጠልለው ይገኛሉ።
መንግስት ሁለት ከተሞች ሙሉ በሙሉ ወድመው እናቶች፤ ከቤት የዋሉ እድሜ ጠገብ አረጋውያን ከነነፍሳቸው ተቃጥለው፤ ምንም አይነት መግለጫ አለማውጣቱና ለችግሩ የሚመጥን ትኩረት አለመስጠቱ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪም ነው።
በአገራችን ላይ የተጋረጠውን ይህንን ሕልውና ተፈታታኝ አደጋ በተባበረና በተጠናከረ ሀገራዊ ትግል ሁሉም የኢትየጵያ ህዝብ ሁሉ አማራ ትግሬ፣ ኦሮሞ ጉራጌ፣ ሃዲያ ከምባታ፣ አፋር ሶማሌ፣ ጋሞ ወላይታ፣ በርታ ሽናሻ፣ አገው ቅማንት ወዘተ… ሳይል ለራሱና ለአገሩ ሕልውና ሲል ሊያወግዘው፤ ሊታገለውና ሊያስወግዘው ይገባል።
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት እንደተለመደው በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ለተጎዱት ወገኖቻችን እንድንደርስላቸው የዕርዳታ ማሰባሰቢያ “ጎ ፈንድ ሚ” የከፈተ መሆኑን እያስታወቅን፤ ወንጀሉን በአንድነት እያወገዝን ወገኖቻችንን እንድንታደግ ጥሪ ያቀርባል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሁን በኋላ በትህነግ/ህወሓትና በኦነግ ሸኔ እያመኻኘ ንጹህ ዜጎች ሲጨፈጨፉ እያለቀስን የመቅበሩ ሂደት መቆም አለበት። መንግሥት ቀይ መስመር ታልፏል የሚልበት ወቅት ስንት ንፁሃን ሲጨፈጨፉ ነው? የሚለውን ጥያቄ ድርጅታችን ያቀርባል። ተከታታይ እልቂት እንዳይከሰት ዋናውን ሃላፊነትና ግዴታ መወጣት የሚገባው በብልጽግና ፓርቲ የበላይነት የሚመራው የፌደራል መንግሥት አመራር መሆኑን እናሰምርበታለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእርስ በርስ መጠፋፋት አባዜ ተላቅቆ እንደቀድሞው በፍቅር፤ በመተሳሰብና በመከባበር ተቻችሎ እንዲኖር እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን አስተዋፆ ማድረግና ለሰላም፤ ለፍትህ፤ ለእኩልነትና ለሁሉም መብት ዘብ ሊቀም ይገባል።
ኢትዮጵያ በአንድነቷና በነፃነቷ ለዘላለም ትኑር!!
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት