የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጨዋታ “ከድጡ ወደ ማጡ” እንደተሸጋገረ ይለፈፋል። ሆኖም፤ ክስተቾችን ከጀርባ ሆነን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ካልተመራመርናቸው ወደ አላስፈላጊ መስመር እንሄዳለን። በፖለቲካ ታሪካችን ያየናቸው ሂደቶች አሉ። ችግሮች በስብሰባዎች፤ በለፈፋና በሰበካ ብቻ ቢፈቱ ኖሮ፤ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ እንደ ኢትዮጵጵያዊያን የሚሰበሰብና የሚለፈልፍ የለም። ችግሮች ድርጅቶችን በመፍጠርና በማፍረስ ቢፈቱ ኖሮ፤ እንደ ኢትዮጵያዊያን የተካነበት አናገኝም። ችግሮች በምሁራንና በልሂቃን ስብሰባዎች፤ “እኔ ከአንተ አላንስም” በሚመስል መረጃ፤ ጥናትና ውይይት ቢፈቱ ኖሮ ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የሚካሄደው ስርዓት አልበኛነት፤ ውንብድና፤ እልቂት፤ ዘረፋ፤ ጽንፈኛነት፤ ዘውጋዊ ብሄርተኝነት፤ ውሸት፤ ጨካኝነትና አገር አፍራሽነት ባልተከሰቱም ነበር። ስብሰባዎቹና ውይይቶቹ ያላስቀደሙት ክስተት፤ ኢትዮጵን፤ ኢትዮጵያዊነትንና የመላውን ኢትዮጵያዊያን ዘላቂ ጥቅም ያለምንም ፍርሃትና ወገንተኛነት አዘውትረው አለማስተጋባታቸው ነው።

ሌላው ቀርቶ በብዙ የሕዝብ መስዋእት፤ በተለይ በወጣቱ ትግል የመጣውን አስፈላጊ ለውጥ ለራሳችን ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም የምናስተጋባው ብዙ ነን። ለውጥ ተካሂዷል ወይንስ አልተካሄደም የሚለው ጥያቄ ተመልሷል። ህወሓት የበላይነቱን አጥቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ለመናገር፤ ለመጻፍ፤ ለመሰብሰብ፤ ለመተቸትና ለመሪዎቻቸው ሃሳባቸውን ያለ ፍርሃት ለመግለጽ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከአሁን በኋላ ለውጡ መሰረት እየያዘ፤ ኢትዮጵያዊና ተቋማዊ እየሆነ፤ ዘርፈ-ብዙ የሆኑትን ተግዳሮቶች እየፈታ ይሄዳል እንጅ እንደገና ወደ አምባገነናዊ ስርዓት ይመለሳል የሚል ፍርሃት የለኝም። ይመለሳል የሚል ስጋት ያለው ግለሰብ ወይንም ቡድን ለውጡን ከሕዝቡ ምኞት፤ ተስፋና ፍላጎት ጋር አላያያዘውም ማለት ነው። ብዙ ሽህዎችን፤ ብዙ ቡድኖችንና ብዙ ተጠቃሚዎችን ያስፈራራው ለውጥ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ኃይሎች ያላቸውን የግንኙነት መረብና ያካበቱትን ግዙፍ ኃብት ተጠቅመው ለውጡን ቢያጥላሉት፤ በተመሳሳይ መቀበል ያለብን ሌሎች በአስርት ሚሊወኖቸ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ደግም እንደሚደግፉት መሆኑን በበኩሌ አምናለሁ።

ለውጡ አልገባንም። ለውጡ የሕዝብ ነው፤ የማንም ቡድን አይደለም። ለውጡን መደገፍ ወይንም አለመደገፍ ከዐብይና ከኢህአዴግ ጋር መያያዝ የለበትም። ግን ተያይዟል። እኔ ለውጡን እድገፋለሁ፤ ስኬታማ እንዲሆንም የተቻለኝን አደርጋለሁ። ለውጡ ተስፋ የሚሰጡ ምልክቶችን እንደሚያሳይ አምናለሁ፤ ለምሳሌ የሰብአዊ መብቶች መከበር፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደም።

በኔ ግምገማና እምነት፤ ከዐብይ የበለጠ ወይንም የተሻለ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ቆርጦ የተነሳ ግለሰብና መሪ የለም። አንድ ምሳሌ ልስጥ። ዐብይ የአጼ ምኒልክን ቤተመንግሥስት እንዲታደስ ያደረገበት ዋና ምክንያት ይህን ቅርስ መላው የኢትዮጵያ አዲስ ትውልድ አይቶ ትምህርት እንዲያገኝበት ነው። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነት ማፍቅረ ማለት ይኼው ነው። እነዚህን እሴቶች የሚያፈቅር መሪ ኢትዮጵያ እንትፈርስ አይፈልግም፤ አይመኝም።

ኢትዮጵያ እንዳትፈራርስ ከፈለግን፤ በአሁኑ ወቅት ከዐብይ ሌላ አማራጭ የለንም። ዐብይ ሰው መሆኑን አንርሳ። መሳያ አይደለም። ሰው ሆኖ ደግሞ በሁሉም ነገር ሙሉ ሊሆን አይችልም። ዐብይ ሃኪም፤ ዐብይ መሃንዲስ፤ ዐብይ ኢኮኖሚስት፤ ዐብይ የፌደራል ፖሊስ፤ ዐብይ ዳኛ ወዘተ ሊሆን አይችልም። ዐብይ ገንዘብ ሊያትም አይችልም። ዐብይ የውጭ ምንዛሬ ሊፈጥር አይችልም። ዐብይ ምሳሌ ወይንም አርዓያ መሆን እንጅ ሁሉን ነገር ዐብይ ይወጣው ካልን ችግሩ የኛ ነው። ኢትዮጵያ የነበረችበትን ሁኔታ ባንረሳ መልካም ነው። ውጭም ሆነ ውስጥ፤ ህብረተሰቡ የለውጡ ደጀን መሆን አለበት።

ይህ እንዳለ ሆኖ፤ ለውጡን መደገፍ ዐብይንና ኢህአዴግን ከመደገፍ ጋር አብረው መሄድ አለባቸው የሚለውን መስመርና መርህ ለመቀበል የምችልበት ምክንያት የለኝም። ከላይ እንደ ጠቀስኩት፤ ዐብይን እንደ ኢትዮጵያ መሪ የምቀበልበት ዋና ምክንያት በሚናገራቸው እሴቶቹና በሚሰራቸው ተግባሮች ነው። ክሁሉም በላይ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ዘላቂነት የማያሻማ አቋም እንዳለው አምናለሁ። በአቋሙም ምክንያት ከየአቅጣጫው የሚወረወርብት የክስ ድንጋይ ብዙ ነው። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነንት ቆመናል የምንል ክፍሎች የድጋይ ውርወራው አካል አንሁን። ገንቢ ሃሳቦች ካሉን በይፋ እናቅርባቸው። አቅም፤ ጉልበትና ፍላጎት ያለን ወደ አገር ቤት ገብተን ስራ እንስራ፤ ሕዝብን እናገልግል። አውቀነውን ሆነ ሳናውቀው፤ ኢትዮጵያን ወደ ታች እየጎተትናት ነው። ብሄርተኝነት ጡፋል። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የኮለጅና የዩንቨርስቲ ተማሪውች በዘውጋቸው መለያ ብቻ እየተመረጡ ትምህርታቸውን እንዳይከተታሉ ተፈርዶባቸዋል። በአክሱም፤ ትግራይ፤ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የትግራይ ብሄር አባል ያልሆኑ ተማሪዎች ከእልቂት ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ በአንድ ላይ

 

ሆነው እንደ “ከብት በአንድ ዶርሚቶሪ ታጉረዋል።” ቁጥራቸው 800 የሚሆን በአዳ ቡልቱ ዩንቨርስቲ፤ ኦሮምያ፤ የሚማሩ አማራዎችና የደቡብ ሕዝብ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች ከአሰቃቂ ግፍ እራሳቸውን ለማዳን ሲሉ በቤተ ክርስትያን ተጠልለዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ፖሊሶችና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ተማሪዎቹን በሰብእነታቸው ከአደጋ በመከላከል ፋንታ ወገንተኛ ሆነዋል። በትግራይ የትግራይ ተማሪዎች፤ በኦሮምያ የኦሮሞ ተማሪዎች ብቻ እየተመረጡ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። ሆነ ተብሎ በሚደረግ ሴራ፤ ተማሪዎች እርስ በእርሳቸው እንዲጋጩ የሚገፉ ኃይሎች አሉ። የክልሉ ባለሥልጣናት እንዴት ሃላፊነት አይወስዱም!! ለውጡ ወደ ታች አልወረደም የሚሉት ተመልካቾች አግባብ አላቸው። ጥናቶችና ምርምሮች የሚያሳዩት፤ የልማት ምሰሶው የሰው ኃብት መሆኑን ነው። በኢትዮጵያና በሌሎች ታዳጊ የአፍሪካ አገሮች የእድገት ተስፋውና ተግዳሮቱ በቁጥሩ እያደገ የሄደውን የወጣት ትውልድ ኃብት እንዴት አድርጎ ለዘላቂና ፍትሃዊ ልማት ለመጠቀም ይቻላል የሚለው ጥያቄ ነው። በመላው አፍሪካ ሲታይ፤ ከ 25 ዓመት እደሜ በታች የሚገመተው የሰው ኃብት 60 በመቶ ነው። የኢትዮጵያም ከዚህ አይለይም። ከአፍሪካ ጠቅላላ ሕዝብ መካከል ከአስራ ሁለቱ አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው። ይህን ግዙፍ የሰው ኃብት በአስቸኳይ ወደ ስራ ዓለም እንዲገባና ምርታማ እንዲሆን ማድረግ ከፍተኛው የፖሊሲ ጥያቄ ሆኗል።

ምን ማለቴ ነው? ኢትዮጵያ በየዓመቱ ሁለት ሚሊየን የስራ እድል መፍጠር አለባት። ካልፈጠረች ግን ይህ ግዙፍ ኃብት ይባክናል። የስራ እድል የሌለው ወጣት ትውልድ መንግሥቱን ያፈርሰዋል።

ከማንኛውም መስፈርት በላይ ወጣቱና ሌላው ትውልድ ደህንነቱ ተጠብቆ በአገሩ ዘላቂነት ማመን አለበት። በዝቅተኛ መስፈርት (Minimum Standard) ስገመግመው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመታደግ ብቻ ሳይሆን፤ የግለሰቦችን ሰብአዊ መብትና ክብር በሕግ ለማስከበር ከተፈለገ በተማሪዎች ላይ የሚካሄድ ጭካኔ መቆም አለበት። ዘውጋዊ ጥላቻና ቂም በቀል በወጣት ተማሪዎች ላይ ሲካሄድ ማየትና ይህን የሚዘገንን ሁኔታ ለማቆም አለመቻል ለክልልና ለፌደራል ባለሥልጣናት አሳፋሪ ነው። ምክንያቱም፤ የሚባክነው የሰው ኃይል የወደፊቱ አምራችና አገልግሎት ሰጭ ኃይል ነው። ውጭ የምኖር ኢትዮጵያዊያንም ይህ ወንጀል እንደሚፈጸም ድምጽ ማሰማት ግዴታችን ነው። ሕገወጥነትና ውንብድና መሰረቱ ምንድን ነው ብሎ አስቸኳይ መፍትሄ መፈለግ ወሳኝ ነው።

በታሪኳ ከቻይና፤ ከፋርስ (ኢራን) እና ከሌሎች ጥንታዊ አገሮች ጋር የምትነጻጸረው ኢትዮጵያ ያጣችው ወይንም ያላገኘችው ክስተት መላውን ኢትዮጵያዊያን በቅንነት፤ በሕዝብ አገልጋይነት፤ አስፈላጊ ሲሆን፤ በደፋርነትና በተጠያቂነት፤ በሃላፊነትና በብልሃት (Political Wisdom) የሚመራት መንግሥት ነው። መንግሥት ስል ከላይ ጀምሮ ወደ ታች፤ እስከ መንደር ድረስ የሚደርስ የባለሥልጣናት መረብ ማለቴ ነው።

ባለፉት አምሳ ዓመታት፤ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ያመረተችው ገዢዎችንና አጥፊዊችን እንጅ አገልጋዮችንና ገንቢዎችን አይደለም። ሊግ ኦፍ ኔሽንስን፤ የተባበሩት መንግሥታትንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሰረተችው እና ጀግኖች ልጆቿ በኮሪያና በኮንጎ ጀብዱ ያሳዩላት ኢትዮጵያ በሁሉም መስፈርቶች ዝቅ፤ ዝቅ እያለች ዛሬ ከደረሰችበት አፋፍ ላይ ደርሳለች። ወጣቱን ትውልድ ለአደጋዎች የምታጋልጥ ሆናለች። የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ከሳሓራ በታች ከሚገኙት አገሮች መካከል አንድ ሶስተኛ ነው። ከአስር ዓመታ በለይ አስደናቂ እድገት አሳይታለች የምትባለው አገር የምግብ ዋስትናን ስኬታማ አላደረገችም። የዐብይ መንግሥት የተረከበው ገቢና የውጭ ምንዛሬ የተሟጠጠ፤ የተዘረፈ ስለሆነ ደሞዝ ለመክፈል አልተቻለም።

የኢኮኖሚው ደካማነት እንዳለ ሆኖ፤ በአብሮነት ታሪክ የሰራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ በፖለቲካ ነጋዴዎች ተበክሎ የዘውግና የኃይማኖት ጥላቻ እንደ ተራ ነገር በማህበረሰባዊ ሜድያ ይስተጋባል። መለያችን ነጻነትና ሰብአዊ ክብር እየተቦረቦረ ሄዶ፤ ሰብአዊ ልእልና፤ብረገባዊነትና አንዱ ለሌላው ወንድሙና እህቱ ማሰብ ሶስተኛ ደረጃ ይዟል። የሞራል ውድመት አገርን ያጠፋል። በተለይ በደርግ የመጨረሻ ዓመታትና በህወሓት መራሹ ኢህአዴግ የተወለደው ወጣቱ ትውልድ፤ ሆነ ተብሎ፤ በአስተሳሰብ እድፍ እንዲበከል ተደርጓል። የብሄርና የኃይማኖት ጥላቻ፤ ስግብግብነት፤ ሌብነት፤ ጨካኝነትና ዘረኝነት እድፍ፤ መርዝና ካንስር ነው።

የኮሌጅ ተማሪ በብሄሩ ብቻ ተመርጦ በዶርሚቶሪው ከተገደለና በክልል ፖሊስ ከተደበደበ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት የሚለው ቀዩ መስመር የት ላይ ነው? ይህ ሁሉን የሕብረተሰብ ክፍሎች እየበከለ የሚታይ የአስተሳሰብ ደዌ ካልተወገደ ዘላቂና ፍትሃዊ ሰላም፤ እርጋታ፤ አብሮነት፤ ልማት እንዴት ይቻላል? ዛሬ በብሄሩ እየተለየ የሚበደለው ዐማራው ብቻ አይደለም፤ የጌድዮ ሕዝብ የውርደታችን ምሳሌ ሆኗል። ይቆያል እንጅ ዘረኝነት ድንበር የለውም።

ሰብአዊ ደህንነት (የመኖር፤ አለመኖር ጥያቄ)፤ ብሄራዊ እርጋታ፤ ለማንኛውም ወንጀል በሃላፊነት ተጠያቂነት ከሌለ ዲሞክራሳዊ ስርዓት ለመመስረት አይቻልም። ዲሞክራሳዊ መንግሥትም ሆኖ በዜጎች መካከል ያለው የገቢና የኑሮ ልዩነት ካልተፈታ ጥላቻና ግጭት አይቀርም። የዚህ ምሳሌ የምኖርበት አገር አሜሪካ ነው። የጥቁሮች ሰብአዊ መብት አሁንም አይከበርም። ሴቶች እንደ ወንዶች አይከፈላቸውም።

ምሁራንና ልሂቃን ማድረግ ያለብን ምንድን ነው? የሚለውን አስኳል ጥያቄ ስጠይቅ የማገኘው መልስ አንድ ነው። ይኼውም፤ ካለፈው የቅርብ አሰቃቂ የፖለቲካ ታሪካችን ተምረን፤ አገራችን ዩጎስላቭያ ወይንም ሶርያ ወይንም ሶማልያ ወይንም ደቡብ ሱዳን እንዳትሆን፤ ምሁራንና ልሂቃን፤ ገዢው ፓርቲና ሌሎች ባለድርሻዎች ከዚህ በፊት ያልሄድንበትን፤ ማለትም የከፋፍለህ ግዛውንና ብላውን የሚያፈራርስና በዜግነት መርህ ላይ የተመሰረተ የአብሮነትን አዲስ መንገድ መከተል ግዴታችን ነው። እንኳን የረዢም ታሪክ ያለን ኢትዮጵያዊያን፤ እኔ የምኖርባት አሜሪካ ከሁሉም ዓለም የተለያዩና የማይተዋወቁ የብሄርና የኃይማኖት አባላትን የሰበሰበች አገር ናት። የፌደራል ስርዓቷ የሁሉንም ዜጎች መብቶች ለማስከበር የሚሞክር ሲሆን፤ በአሜሪካ የቀን ተቀን ጉዳዮችን በመንደርና በአካባቢ ደረጃ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድረው ሕዝቡ ነው። ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች የሚስተናገዱት በተራው አሜሪካዊ ነው። ሆኖም፤ አሜሪካኖች ልዩነቶች ሳይበክሏቸው ለብሄራዊ አንድነታቸው ተሟጋቾች ናቸው። የሚያስቀድሙት አሜሪካንና የአሜሪካን ዜግነት ነው። እኛ ይህን ለማድረግ የማንፈቅድበት ምክንይት ምንድን ነው? ታሪክ አለን ካልን ታሪክን ለመስራት እንድፈር። ድህነትን ለመቅረፍ እንተባበር።

የአሜሪካ ዲሞክራሲ ያልፈታውና እንዲያውም ያባባሰው አስኳል ክስተት ግን በዜጎች መካከል እየሰፋ የሄደውን የገቢና የኑሮ ልዩነት ነው። ስለዚህ፤ ዲሞክራሲም ስንል ምን አይነት ዲሞክራሲ እንደሚሆን አስቀድሞ መወያየት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የራሱን ልጆች ለማገልገል ከፈለገች መጀምሪያ ዜጎቿንና እሴቶቿን አክብራ ታስከብር። በዚህም መስፈርት ስመለከተው ዐብይ የሚናገረውና የሚሰራው የኢትዮጵያዊያንን ክብርና ቦታ ለማጠናከር ሆኖ አገኘዋለሁ።

ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት እኛ ስንጓዝበት የቆየነው መንገድ ዘውጋዊነት ነው። ያፈረስነው መንገድ በዜግነት የተመሰረተውን የኢትዮጵያዊነትን ማህበረሰባዊ ሰንሰለት ነው። የጋራ ችግሮቻችን በጋራ ለመፍታት ከተፈለገ፤ ያልሄድንበት መንገድ ዘውጋዊነት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። በዜግነት መብቶች መከበር ላይ የተመሰረተ በሕግ የበላይነት ብቻ የሚተዳደር ሌላ የፌደራል ስርዓት መመስረት ነው። አሜሪካን ኮርጀን፤ አሜሪካን እንሁን ማለቴ አይደለም። ከራሳችን ባህል፤ ልምድና ታሪክ ጋር የሚዛመድ ማህበረሰባዊ ዲሞክራሲ ማለቴ ነው።

ከስሜት ውጭ የሆኑ መስፈርቶችን ተጠቅመን ብንመራመር፤ ብሄር ተኮሩ ስርዓት አገር እያፈረሰ ነው። እኔን የሚያሳስበኝ፤ የኢትዮጵያ ምሁራን፤ ልሂቃንና የመንግሥት ባለሥልጣናት የማያዩትና የሚፈሩት ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣኑ ባለቤት ከሆነ የኔና የኔ ዘውግ ሚናና ጥቅም ይፈርሳል የሚለው ስር እየሰደደ መሄዱ ይታያል።

ከሩብ ምእተ አመታት የእርስ በእርስ ግጭት፤ አፈናና ምዝበራ በኋላ በዘውግና በቋንቋ የተመሰረተው የፌደራል ስርዓት ይሰራል ብሎ መስበክ “ዶሮን ሲያታልሏት” ሆኗል። ተራው ኢትዮጵያዊ የስርአቱ ተጠቂ እንጂ ተጠቃሚ አልሆነም። ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ የተከለው የዘውግ ጥላቻና የመከፋፈል መርዝ ሕብረተሰቡን በክሎታል። አንድ ለአምስት የሚለው የአፈናና የምዝበራ መዋቅር የፈረሰ ይመስላል እንጅ ሰንሰለቱ አልተበጠሰም። ለውጡን አንፈልግም የሚሉት ኃይሎች እየተስፋፉ የሄዱበት ምክንያት ሁሉም የሚሻማው ለኢትዮጵያና ለመላው መቶ አስር ሚሊየን ሕዝቧ ሳይሆን፤ ለራሱና ለቡድኑ ጥቅም ቀጣይነት ነው። ለማሳሰብ የምፈልገው አስኳል ጉዳይ፤ የተበታተነ ሕዝብ ድሃና ኋላ ቀር እንደሚሆን ነው። ድሃና ኋላ ቀር ሕዝብ ደግሞ ለማፈንና ከፋፍሎ ለመግዛት ያመቻል።

በአሁኑ ወቅት የሚካሄደው ዱላና ክላሽ ብቻ የቀረው ግብግብና ክርክር በሁለት መስመሮች መካከል ነው። በአንድ በኩል ለውጥ እየተካሄድ ነው በሚሉትና በሌላ በኩል ምንም አይነት ለውጥ አይካሄድም በሚሉት መካከል። የመስመር ልዩነት መኖሩ ጤናማ ነው። ጤናማነቱ አከራካሪና ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝነው ግን ውይይቱ በሃሳብ ልዩነት ላይ ሳይሆን በግለሰቦች ሰብእነት ዙሪያ ሲሆን ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ቀይ መስመር ወይንም የትራፊክ ምልከት አናበጅም። ጠ/ሚንስትሩን በስም እያነሱ መስደብና መወንጀል ለኢትዮጵያ ምን ፋይዳ አለው?

በኢትዮጵያ ለውጥ አለ ሲባል እኔn የሚገባኝ ምልክቶች መኖራቸው እንጅ ሁሉም ነገር ተሳክቷል የሚለው አይደለም። የመቶ አስር ስብጥር ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት የተለያየ ነው። ሁሉንም ክፍሎች በአንድ ወቅት ለማስደሰት አይቻልም። እኔ ለውጥ አለ ብየ እከራከራለሁ። ለምሳሌ፤ ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት በማይታሰብ ደረጃ ሕዝብ በነጻነት ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጋል። መንግስትን የመተቸት መብት አለ። ከጎረቤት አገሮች ጋር ጠንካራ ግንኙነት እየተፈጠረ ነው ወዘተ. ይህ ለውጥ ነው።  በተመሳሳይ ደረጃ ሊካድ የማይችል ሃቅ አለ። ሙሉ ሰላምና መረጋጋት የለም። ሕዝብ ከቀዩ ፈልሷል። ኢትዮጵያ ግን አልፈረሰችም። ፈርሳለች የሚል ግለሰብ ወይንም ቡድን መረጃ የማቅረብ ግዴታ አለበት።

ሚዛናዊ ለመሆን ሁሉም ነገር “ጨለማ ነው” ለማለት የሚያስችል መረጃ የለም። የለውጡን ኃይል በመተቸትና ለውጡ ተግዳሮቶች ገጥመውታል በሚለው መካከል ሚዛናዊ የሆነ ትንተናና አማራጮችን ማቅረብ ያስፈልጋል። የመተቸት ልምዳችንና ባህላችን መቀየር አለበት።

መታረቂያ ወይንም የሚያስማማ ሃሳብ ማቅረብ ለውጡ ወደ ዲሞክራሲ እንዲሸጋገር ይረዳል። “የኔ ሃሳብ ብቻ” የሚለው መስመር ግን ለዲሞክራሲ መቅሰፍት ነው። “የኔ ብቻ” ከሆነ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም፤ ይሰረቃል።

ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ኢትዮጵያን ለዚህ አደገኛ ሁኔታ ያደረሳት ጠባብ ብሄርተኛውና እብሪተኛው ህወሓት ሶስት ነገሮችን ቢያደርግ ይመረጣል።

አንድ፤ ለትግራይ ሕዝብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመናገር፤ ለመንቀሳቀስ፤ መሪዎቹን ሆነ የሚከተሉትን ፖሊሲ ለመተቸትና ከሌላው ወንድሙና እህቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለመወያየት ነጻነት ይሰጠው። የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። ኢትዮጵያዊነቱን የነጠቀው ቡድን ህወሓት ነው። የማሰምርበት ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የአንድ ሳንቲም ግልባጭ አለመሆናቸውን ነው። የትግራይን ሕዝብ ከዐማራው ሕዝብ ጋር ያናከሰውና ወደ አላሳጊ ጦርነት የሚገፋው ህወሓት ነው። የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ቢያስወግድ ሌላው ሁሉ የፖሊሲ ጥያቄ በሰላም፤ በውይይትና በድርድር ይፈታል፤ ለምሳሌ፤ የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ራያና ሌሎች ቦታዎች ጉዳይ። የማይፋታን ሕዝብ ተፋታ ብሎ መወሰን ድንቁርና ነው።

ሁለት፤ የህወሓት አመራር ከዐብይ መንግሥት ጋር በግልጽ መወያየት አለባቸው። ህወሓቶች የፌደራሉን መንግሥት እንደ ጠላት ማየታቸውን ማቆም አለባቸው። ወንጀለኞችን መደበቃቸውን ማቆም አለባቸው።

ሶስት፤ ህወሓቶች አንቀጽ 39ን (በተለይ መገንጠልን) መሳብ አለባቸው። እንገንጠል ብለው ከወሰኑ ግን ውሳኔያቸውን ለትግራይ ሕዝብ ያቅርቡና ሕዝቡ ድምጽ ይስጥበት። እኔ የትግራይ ሕዝብ መገንጠልን ይመርጣል የሚል ስጋት የለኝም። ትግራይ የኢትዮጵያ ታሪካዊ አካል መሆኑን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል።

ራሳቸው የፈጠሯቸውን ችግሮች ገና ሳይፈቱ፤ ህወሓቶች “ምርጫው መተላለፍ የለበትም” ይላሉ። የትግራይ ሕዝብ መብት ስለታፈነና የትግራይ ሜድያ የህወሓትን መስመር ስለሚያስተጋባ፤ ሕዝቡ በነጻነት ለመወያየት አልቻለም። ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሊኖረው የሚገባው ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ግንኙነት ተቋርጧል። የታፈነ ሕዝብ ምርኮኛ ነው። ስለሆነም፤ ምርጫ ቢካሄድ አንድ ወጥ ስለሆነ የሚመርጠው ህወሓትን ነው። በሌላው ኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ ግን አንድ ወጥ አይደለም። በግጭት ተበክሏል። በአገሩ ውስጥ ስደተኛ የሆነው ብዙ ሚሊየን ይገመታል። ስለዚህ፤ ምርጫ ቢካሄድ ተጠቃሜ የሚሆነው ህወሓት ነው። የሚያደፋፍረው በመላው ኢትዮጵያ የዘረጋው የጥቅም መረብ ነው።

የለውጡ አወንታዊ ግኙቶች እንዳሉ ሆነው፤ አንድ አገር አለን ብሎ ለመናገር የማይቻልባት ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ተግዳሮቶች ገጥመዋታል።

መፍትሄው ምንድን ነው?

በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ለምናምን ዜጎች፤ ዛሬ የሚያስፈልገው የፖለቲካ ጨዋታ ከይስሙላ ምርጫ በፊት፤ ብሄራዊ መግባባትብሄራዊ ሰላምና እርቅ፤ የጋራ ወይንም ብሄራዊ ራእይ፤ ብሄራዊ የመካከለኛና የመካለለኛና የረዢም ጊዜ ፍኖተ ካርታ እና ኢኮኖሚው ከገጠመው ከፍተኛ ተግዳሮት እንዲላቀቅ አስተዋፆ ማድረግ ነው።

ሰማንያ አገሮች የሉንም፤ ያለችን አንዲት አገር ናት። ይህችም አገር ኢትዮጵያ ትባላላች። ከየት ጀምረን ወደ የት እንደምንሄድ ካላወቅን፤ አሁን ያለው ሁኔታ ይባባሳል። በኔ አድሜ አካባቢ የነበርን ግለሰቦች የማናውቃቸው የጥቁር አፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያን አልፈዋታል። ሞሪሽየስ፤ ናምቢያ፤ ሴሸልስ፤ ኬፕ ቨርዲ፤ ደቡብ አፍሪካ በመልካም አስተዳደር፤ በሰብአዊ እድገት፤ በነፍስ ወከፍ ገቢ ቀድመውናል። በደህነትና በጸጥታ፤ በሕግ የበላይነት፤ በዜጎች ተሳትፍኖና በሰብአዊ መብቶች መከበር፤ በዘላቂና በፍትሄያዊ እድገት፤ በነፍስ ወከፍ ገቢ፤ በአካባቢ ደህንነት ወዘተ ከኢትዮጵያ ይበልጣሉ። ኢትዮጵያዊያን ወደነዚህ አገሮች የሚሰደዱበት ዋና ምክንያት ልማታቸው ከፍተኛ ስለሆነ እንጅ አገራቸውን ጠልተው አይደለም።

እኛ ግን ዛሬ በዘውግ ልዩነቶች፤ በስግብግብነት፤ በመሬት ሽሚያ ላይ እያተኮርን፤ ኃብት እያወደምንና ፍትሃዊና ዘላቂ እድገትን እየጎተትን ነው። የምንጨቃጨቀው ስላለፈው መጥፎ ታሪክ እንጅ፤ ስለወደፊቱ መልካም ራእይና ተልእኮ አይደለም። አክራሪነት ከመቸውም በባሰ ደረጃ ስር እየሰደደ ነው። ሥልጣን ፈላጊነት ልክ የየካቲትን አብዮት ይመስላል። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁሉም አዋቂ፤ ሁሉም ትችት አቅራቢ፤ ሁሉም ሌላውን ተቃዋሚ ሆኗል። አንዱ ከሌላው መማርን ንቆታል። በዘውጎች ልሂቃን ወይንም ድርጅቶች መካከል የሚደረግ የአብሮነት ውይይት የለም። እያንዳንዱ ግለሰብና ቡድን የሚያስተጋባው አጀንዳ የለውጥ ተቃውሞዎችን ሆኗል። የተቃዋሚዎችን ብሂል ማባዛት ራሱ ችግር ሆኗል። ሁሉም አዋቂ ስለሆነ፤ መደማመጥ፤ መመካከርና መናበብ የሚባል ጉዳይ የለም። የፖለቲካ ንግድ ተፋፍሟል ያልኩት ለዚህ ነው።

በደርግ መንግሥት ብሄራዊ ባንክን ወክየ ናይሮቢ ሄድኩ። ሱቆችን ስመለከት ባለቤቶቹ በሙሉ ፈረንጆችና ኤዢያዊያን ነበሩ። ከአንድ ኬንያዊ ኢኮኖሚስት ጋር ስንነጋገር እንዲህ አለኝ። “እናንተ ኢትዮጵያዊያን እኮ ታኮራላችሁ። አዲስ አበባን የመሰረታችኋት ራሳችሁ። አብዝኛውን ሱቅ በባለቤትነት የያዛችሁት ራሳችሁ። የምታኮሩት ለዚህ ነው።” እኔም በአገሬና በአዲስ አበባ የምኮራው ከተማዋን የመሰረቷት ፈረንጆች ሳይሆኑ ኢትዮጵያዊያን በመሆናቸው ነው። አዲስ አበባ የነጻነት ተምሳሌት ናት። ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን ቀና አድርገው “የኛ ከተማ ናት” የሚሉት ትክክል ነው።

በተጨማሪ፤ አዲስ አበባ ከሌሎች የአፍሪካና የኤዢያ ከተማዎች የተለየች ናት። ከንው ዮርክ፤ ከጀኔቫና ከቬና ውጭ ብዙ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፤ የዲፕሎማቲካ ስብስቦች፤ የመንግሥት ያልሆኑ ተቋማት የሚገኙባት ከተማ አዲስ አበባ ናት። ሁሉም የኢትዮጵያ ዘውጎችና ኃይማኖቶች አባላት የሚኖሩባት ከተማ አዲስ አበባ ናት። ይህች ከተማ የወደፊቷን የምንመኛትን ኢትዮጵያን ሆናለች ብል አልሳሳትም። ገጠሬነትን ካልመረጥን በስተቀር ከተሜነት አይቆምም። ከተሜነት ደግሞ ሁሉም ዜጎች የሚኖሩበት መሆኑ አይቀርም። ጎንደር፤ ባህር ዳር፤ ድሬ ዳዋ፤ አዋሳ ተመሳሳይ ስርጭት በማሳየት ላይ ናቸው። ከተሜነት እየተስፋፋ ሲሄድ በዜጎች መካከል ያለውም የብሄርና የኃይማኖት ልዩነት እየጠበበ ይሄዳል።

ታዲያ ይህች ከተማ ለምን እንደ ዋሺንግተን ዲሲና እንደ አቡጃ፤ እንደ ዴልሂና እንደ ብራዚሊያ ራሷን ችላ በነዋሪዎቿ የተመረጡ አስተዳዳሪዎቿን ለመሰየም ትችላለች ለማለት እንፈራለን? ከተሜነት በፖለቲካ ፓርቲ አይመራም።

በአንድ በኩል ዲሞክራሲ ያስፈልጋል እያልን፤ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት የለውም የምንል መኖራችን ለኔ ያሳስበኛል። አዲስ አበባን እንደ ምሳሌ የተጠቀምኩበት ዋና ምክንያት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መኖሪያ በሆነችው በአዲስ አበባ ሁኔታ ላይ ለመስማማት ካልቻልን በሌላው የአስተዳደር ሁኔታ ለመስማማት አስቸጋሪ ሆኖ ስላገኘሁት ነው።

የአዲስ አበባም ሆነ ሌሎች ክስተቶች ለውጥ በሚካሄድበት አገር ሁሉ ይኖራሉ። ግን፤ ለውጥ ሲካሄድ መልካሙን ውጤት ከመጥፎው ለመለየት ካልቻልን፤ ለውጡ ወደ አጥፊነት እንዲያመራ ግብዓት እንደምናደርግ ማሰብ ግዴታችን ነው። የለመድነው የፖለቲካ ባህል ግጭት፤ ስድብ፤ ግድያና አፈና ስለሆነ ሳናስበው ለውጡ ወደ አምባገነናዊ መንግሥት እንዳይመልሰን ወይንም ኢትዮጵያ ዩጉስላቭያን እንዳትሆን ማሰብ አለብን። ይህች አገር የጦርነት አውድማ እንድትሆንና እንድትፈርስ የሚፈልጉ የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን የረሳን ይመስለኛል። ለውጡ ስለ ዐብይ አይደለም። ለውጡ ስለ ኢትዮጵያና ስለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ዐብይ ድልድይ ነው። ዐብይ አመቻች ነው። ይህን ካወቅን ከወገንተኝነት ይልቅ ለጋራ አገርና ለጋራ ሕዝብ መታገሉ ይሻለናል።

ወደ የት ለመሄድ እንፈልጋለን የሚለውን አስኳል ጥያቄ ለመመለስ የምንችለው ለጋራ አገርና ለአንድ ሕዝብ በሚጠቅም በሕዝባዊ ውይይት ነው። በአድማ፤ በሴራ፤ በስድብ ናዳ፤ በውንብድና፤ በመሸሺ፤ በአመጽና በጦርነት ሊሆን አይችልም። የፖለቲካ ልሂቃን ብቻቸውን ለውጡን ስኬታማ ሊያደርጉት አይችሉም። ሕዝባዊ ውይይት፤ ሕዝባዊ እርቅና ሰላም ያስፈልጋል። ተቋማት ወሳኝ ናቸው። የሕዝቡ ድምጽ ግብዓት ይሁን እላለሁ። አገር አቀፍ ሕዝባዊ ውይይት ይካሄድ!!

ኢትዮጵያን የሚያድናት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና ፍትህ ብቻ ነው። በአሁኑ ወቅት፤ ሌላው ቀርቶ የውጭ ተመልካቾችና ታዛቢዎች አገሪቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሷን ይናገራሉ። ሕወሓት መራሹን የኢህአዴግን መንግሥት የተካው የኦሮሞ ዴሚክራሳዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የበላይነቱን መያዙን የሚያመለክቱ ብዙ መረጃዎች ይቀርባሉ። ግን፤ ዝርዝሩን ስታስቲክስ በሚገባ ስለማናውቀው፤ ከዚህ ስሜታዊ ድምዳሜ ብንጠነቀቅ ይሻላል። እኔ ዐብይ አድሏዊ ስርጭትን እንደ ፖሊሲ ይከተላል የሚል መረጃ ለማግኘት አልቻልኩም። አፍራሾች የሚሉትን ደግሞ ለመቀበል አልችልም።

ጥርጣሬና ስጋት መኖሩ ይገባኛል። ትላንት ህወሓት የፖለቲካውንና የኢኮኖሚውን የበላይነት ይዞ እንደ ነበር ሊካድ አይችልም። ትላንት በብዙ ሽህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እንደ ተጨፈጨፉ ወይንም እንደ ታሰሩ ወይንም ከቀያቸው እንደተባረሩና እንዲሰደዱ እንደተደረጉ አይካድም። ትላንት ከደቡብ፤ ከጋምቤላ፤ ከኦሮምያ፤ ከቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ ከአማራ ክልል ወገኖቻችን በገፍ እንደተባረሩ ይታወቃል። ትላንት ብዙ ቢሊየን ዶላር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ተሰርቆ ከአገር እንደሸሸ አይካድም። ትላንት ምርጫ ተካሂዶ ገዢው ፓርቲ እንዳሸነፈ፤ ቅንጅት/ህብረት ቢያሸንፉም ምርጫው እንደተሰረቀ፤ ብዙ ወጣቶች እንደተጨፈጨፉ አይካድም። ጥንቃቄ ካልተደረገ በስተቀር፤ ይህ ሁኔታ እንደሚደገም አሳስባለሁ። የምርጫ ቦርድ ሁኔታውን ሚዛናዊ በሆነ መስፈርት ገምግሞ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ቅድመ ሁኔታዎችን ቢያመቻች ይመረጣል።

ትላንት የስልጣን ባለቤት የነበረው ህወሓትና አጋር ድርጅቶች ተመካክረው የኢትዮጵያን የባህር በር እንዳዘጉት ሊካድ አይችልም። ሌላውን ሁሉ አስኳል ጉዳይ ብንረሳው ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣቷ ለደህንነቷና ለልማቷ አስጊ ሁኔታ መፍጠሩ ህወሓትን ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግን በሙሉ በታሪክ ሲያስወቅሰውና ሲያስጠይቀው እንደሚቆይ አይካድም። ትላንት በቋንቋና በብሄር የተዋቀረው ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያን ከመቶ ዘጠና አምስት አገሮች መካከል ብቸኛዋ የብሄር ተኮር አገር እንዳደረጋትና እያንዳንዱ ክልል ለራሱ አካባቢና ዘውግ ወገንተኛነት እንጅ ለአገሪቱና ለኢትዮጵያዊነት ታማኝ እንዳይሆን እንዳደረጋት ይታወቃል። ፌደራላዊ አገዛዝ የምትከተለው ናይጀሪያ የፌደራልና የክክል ባለሥልጣናት ሁሉ የመጀመሪያ ታማኝነታቸው ለናይጀሪያ መሆኑን በሕግ ደንጋገለች። ዘረኛነትና ዘውጋዊ ብሄርተኝነት የድህነት፤ የአገር መፈራረስ መጋቢ መሆኑን ከቢያፈራ ጦርነት ልምዳቸው ተምረዋል። ኢህአዴግ ከሰራው ስህተት አልተማረም።  ዛሬም ቢሆን እንደ ትላንቱ፤ ኢትዮጵያ የተመሰረተችው በቅኝ አገዛዝ እንጅ በዜጎቿ ፍላጎትና ፈቃድ አይደለም የሚሉ ኃይሎች አገሪቱን እንዳትረጋጋና እንድትበታተን አስጊ ሁኔታዎችን ፈጥረውባታል። አለመረጋጋቷን የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ክፍተቱን ለራሳቸው ብሄራዊ ፍላጎት እየተጠቀሙበት ነው። በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ የሚካሄደው ቀውስ ምሳሌ ነው። መሳሪያ እንደ ልብ የሚሰራጨው የትኛውን የውጭ ጠላት ለመዋጋት ነው?

ባለፉት 28 ዓመታት ይህ ሁሉ ግፍና በደል ተካሂዶ፤ ብዙ ወንጀለኞች አሁንም በሃላፊነት ለፍርድ አልቀረቡም። የትግራይ “ክልል” የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 39ን መሰረት አድርጎ ከአንድ ዓመት ወዲህ የሚካሄደውን ሰላማዊ ለውጥ አሻፈረኝ በማለት መቀሌ መሽጓል። ወንጀል የፈጸሙትን ለፌደራሉ መንግሥት ላለማስረከብ ወስኗል። ይህ ሁኔታ በዋናነት የሚጎዳው የትግራይን ሕዝብ ነው። ህወሓት መሸነፉ ሊዋጥለት አልቻለም።

ለዚህ ትንተና አግባብ ያለው አስኳል ጉዳይ ግን፤ ህወሓትና ኦዴፓ በተመሳሳይ ደረጃ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ መንግሥት መርህ (የሚመራው) ልማትና በቋንቋና በዘውግ የተዋቀረው ሕገ መንግሥት ለድርድር አይቀርቡም” ማለታቸው ነው። እኔ የምከራከረው እነዚህን መርሆዎች ይዘን ፍትሃዊና ዘላቂ ልማት ስኬታማ ለማድረግ አንችልም ነው።

ይህን ስል ግን መንግሥት በኢኮኖሚው ሚና የለውም ማለቴ አይደለም። ፓርቲዎች ግን በቀጥታም ሆነ በተዘውዋሪ የኢኮኖሚ አንቀስቃሽ ሞተር መሆን የለባቸውም። መንግሥት ቅድሚያ ለግል ክፍሉ ሰጥቶ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ሚና አለው። የሕዝብ የሆኑትን ድርጅቶች የግል ማድረግ አለብን የሚለው መርህ በጥንቃቄ መካሄድ አለበት። የኢትዮጵያን አየር መንገድ የግል ማድረግ ትክክል አይደለም። ሌሎችም የሕዝብን ጥቅም በሚጎዳ መስመር መካሄድ የለባቸውም።

ኢትዮጵያ አፍሪካን ካደኸያትና ወደ ኋላ ካስቀራት ከአይኤምኤፍ መዋቅራዊ ማስተካከል ፖሊሲ (Structural Adjustment) ራሷን መጠበቅ አለባት። የሕዝብ ኩባንያዎች የግል ሲሆኑ፤ በአብዛኛው የሚጎዳው ድሃውና ሰርቶ አደሩ ሕዝብ ነው።

ለሁሉም ብሄራዊ ጉዳይ ሕዝብን ማማከር ወሳኝ ነው።

ዐብይ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆን ሁኔታውን ያመቻቸለት ኃይል ወጣቱ የከፈለው መስዋእት ነው። ኢህአዴግ ፈልጎና ፈቅዶ ያመጣው ለውጥ አይደለም። ይህ ወጣት ትውልድ የሚፈልገው እድገትን፤ ፍትህን፤ የስራ እድልን ነው። ጠ/ሚንስትሩ ሃላፊነቱን ከተረከበ በኋላ የኢትዮጵያን ሕዝብ የማረከውና ተስፋ የሰጠው የፖለቲካ ክስተት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አጠናክሮ ማስተጋባቱ ነው። አገርና ሕዝብ ወዳድ መሆኑን የሚያሳየው ሌላው ቀርቶ፤ በቅርቡ ሱዳን ለጉብኝት ሂዶ ሲመለስ ታስረው የነበሩትን ኢትዮጵያዊያን አስፈትቶ ራሱ በተሳፈረበት አውሮፕላን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉ ጭምር ነው። ይህ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት ነው። ዐብይ አገር ወዳድ መሆኑን አልጠራጠርም።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከአሁኑ ዘውጋዊና ክልላዊ መለያ ጋር አብረው አይሄዱም። ዘላቂና ፍትሃዊ ልማት ከአብዮታዊ ዲሞክራሲና ከመንግሥት መር ልማት ጋር አብረው አይሄዱም። መሰረታዊ፤ ተቋማዊና አገራዊ (ብሄራዊ) ለውጥ ያስፈልጋል የሚለውን መሰረተ ሃስብ በተደጋጋሚ ስላቀርብኩ አልደግመውም። ላሰምርበት የምፈልገው ጉዳይ ግን፤ ለውጡ ከተካሄደ ከዓንድ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ በተፈለገው ደረጃ የተቋማት ለውጦች አላደረገችም። ከእነዚህ መካከል እኔን የሚያሳስበኝ የኢትዮጵያ የመከላከያ፤ የደህንነትና የፌደራል ፖሊስ ገና ብሄራዊ ወይንም ኢትዮጵዊ አለመሆናቸውና ከአገሪቱ የደህንነት ክፍተትና ፍላጎት ጋር አለመመጣጠናቸው ነው። እነዚህ ተቋማት ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ወሳኝ ናቸው። ኢትዮጵያ እንደ ዩጎስላቭያ ከፈራረሰች ሰላም፤ እርጋታ፤ ልማት፤ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም። ማንም ዜጋ ተጠቃሚ አይሆንም።

በጎንደር፤ በሰሜን ሸዋ፤ በጋምቤላ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ በደቡብ፤ በኦሮምያ፤ በአዲስ አበባና በአካባቢዋ በተከታታይ ሲካሄድ የቆየው መፈናቀል፤ ግድያ፤ የባንኮች ዘረፋ፤ ሕገ ወጥነት፤ የመሳሪያ ዝውውርና ሽያጭ፤ የዜጎች በሰላም ወጥቶ ለመግባት አለመቻል ወዘተ የሚያሳየው የማይካድ ክስተት አለ። ይኼውም የፌደራሉ መንግሥት ተቋማትን ለመገንባት አለመቻሉ፤ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ፍኖተ ካርታ አውጥቶ፤ የተግባሮች ቅደም ተከተሎችን ስትራተጂክ በሆነ መንገድ ቀይሶ አገሪቱን ለማስተዳደርና ሕዝቡን ለማገልገል አለመቻሉ የሕዝብ እምነት እንዲበረዝ አድርጎታል። ፍኖተ ካርታ እስከ ምርጫው ድረስ መቆየት የለበትም። ግብጽ ዲሞክራሳዊ መንግሥት አላት የላትም። ግን፤ እስከ 2030 ድረስ የአገሪቱን ልማትና ደህንነት የሚመራ ፍኖተ ካርታ አውጥታ ትጠቀማለች። ትኩረቷ ሁሉን አቀፍ ከሆነ፤ ከፍትሃዊ ልማት ላይ ነው።

ኢትዮጵያ በካድሬዎች መመራቷ ካልቆመ ልማቷ ስኬታማ አይሆንም።

ኢትዮጵያ ባለሞያዎች የሚከበሩባት አገር አይደለችም። ብዙ የህክምና ባለሞያ የምትፈልግ አገር ለባለሞያዎች ደህንነት መቆም አለባት። የኢትዮጵያ ባለሞያዎች አግባብ ባለው ስራ ላይ እንዲሰማሩ አይደረግም። የተሰማሩትም የበላያቸው ካድሬ አያሰራቸውም። እንደ ቱሪዝም ባሉ መስሪያ ቤቶች፤ ባለሞያዎችና ሌሎች ልምድ ያላቸው ሃላፊዎች ስራቸውን እየለቀቁ ነው። የዚህ አይነቱ አስራር መታረም እስከ ምርጫው ድረስ ሊቆይ አይችልም።

ምክንያቱም፤ በተደጋጋሚ የሚነገረው ክስተት፤ የስራ አፈጻጸም ድክመት አገሪቱን ጎድቷታል፤ ባጀት እየከሰረ ነው የሚሉት ታዛቢዎች ብዙ ናቸው፤ ፈረንጆችን ጨምሮ። ውሳኔ ለነገ የሚባልበት ምክንያት ምን እንደሆነ አይገባኝም።

ትኩረቱ ምን ላይ ይሁን?

ከሶት ሚሊየን ሕዝብ በላይ መልሶ ማቋቋም ጊዜ እንደሚወስድ አምናለሁ፤ ግን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። መፈናቀል እንዳይደገም ችግሮችን ከሕዝብ ጋር በመወያየት መፍታት ያስፈልጋል። በየአካባቢው ከሕግ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት ጊዜ የማይሰጠው አገራዊ ጉዳይ ስለሆነ በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ የህልውና ጥያቄ ሆኗል። የውጭ መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በሕግ መከልከል አለበት። መሳሪያ የሚሸጡ አገሮችም ንግዱን እንዲያቆሙ የዲፕሎማቲክ ጫና መደረግ አለበት።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የዘውግ ልሂቃን፤ የክልሎች የበላዮችና ደጋፊ ምሁራን ብሄርንና አገርን በተመሳሳይነት ያያሉ። ይህ የህወሓትና የኦነግ የዘውጋዊነት የፖለቲካ ባህል መተካት ያለበት በሌላ ዘመናዊነትን፤ አብሮነትን፤ ፍትህን፤ እውነተኛ እኩልነትን በሚያጠናክሩ ባህሎችና ልምዶች መሆን አለበት። ቦትስዋናን ለመሆን ከተፈለገ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በዜግነት መብት ላይ መረባረብ ግዴታው ነው። ዘውጋዊ አስተሳሰብ ይዞ ደቡብ ኮሪያን ወይንም አሜሪካን ወይንም ጀርመኒን ወይንም ቻይናን ለመሆን አይቻልም። ልማትና ዘረኝነት፤ እድገትና መንደርተኝነት አብረው የሄዱበት ሕብረተሰብ ለማግኘት አይቻልም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያምርበት ሲተባበር ብቻ ነው።

የዘውገኝነት ፖለቲካ ባህል በአዲሱ ትውልድ ልክ እንደ ተራ ነገር እንዲዛመት ተደርጓል። ይህ ለወጣቱ ትውልድ አጥፊና አድካሚ መሆኑን ማሰብና ሰፊ የአስተሳሰብና የባህል ለውጥ እንዲዛመት ማድረግ ታሪካዊ ግዴታችን ሆኗል።

ዘውግ ወይንም ክልል ማለት ኢትዮጵያ ማለት አይደለም። የትግራይ ወይንም የዐማራ ወይንም የኦሮምያ ወዘተ ክልል ራሱን የሚገመግመው እንደ ተለየ አገር ሆኗል። ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ተራው የኔ ብጤ ግን በቀን ሶስት ምግብ መብላት ካቆመ ቆይቷል። ክልላዊነት ያደክማል፤ ያደኸያል። የክልላዊነት አስተሳሰብና ስሌት መቆም አለበት የምለው ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ነው። እያንዳንዱ ዜጋ የህወሓትን/ኦነግንና የሌሎችን ዘውጋዊ ስሌት ከተቀበለ፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ማን ሊታገል ነው?

በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው ክፍል መጠንቀቅ ያለበት፤ ህወሓታዊና ኦነጋዊ አስተሳሰብ ይዞ ኢትዮጵያን ከአደጋ ለማዳን እንደማይቻል ነው።

ዘውጋዊነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጋጭቷል። ምሁራን በጋራ ሆነው ይህን አቋም ካልታገሉት ሚናቸው ምንድን ነው?

 

ሁሉም አለቃ በሆነባት ኢትዮጵያ “ሁለት መንግሥታት አሉ” ተብሎ የሚናፈሰው ዘውጋዊነት ስር ስለሰደደ ነው። የዚህ “የሁለት መንግሥታት” ክስተት ወሰኑ ትግራይ ብቻ አይደለም። ሃያ የባንክ ቅርንጫፎች በቀን ሲዘረፉ የክልሉ ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ያልደረሰበት ምክንያት ለምንድን ነው? ዝርፊያው በተካሄደበት አካብቢ የሚገኙት የክልል ባልሥልጣናትና አዲስ ፊታውራሪዎች ሽፋን ሰጥተው ይሆን ብለን መጠየቅ አለብን።

አግባብ ባለው መስፈርት ብንለካው፤ በክልሎችና በፌደራሉ መንግሥት ማካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ አይደለም። ብቃት ያለው የፌደራል መንግሥት የመጀመሪያ ሚናውና የብቃት መስፈርቱ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነትና የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ደህንነት ማስከበር ነው።

ባጭሩ፤ ጽንፈኛነት ለኢትዮጵያ አደገኛ ነው።

አል ሸባብ፤ አልካይዳና የመሳሰሉ ኃይሎች ጽንፋዊነት ለኢትዮጵያ አስጊ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር አስቀድሞ ማሰብና እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። የግብጽ መንግሥት ከጠባብ ብሄርተኞች ጋር እየተመሳጠረ የሚያካሂደውን ሴራ አስቀድሞ መከላከል ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነው። ግብጽ የራሷን ጥቅም ለማስከበር፤ በተለይ ታላቁን የተሃድሶ ግድብ እንዳይሳካ ለማድረግ፤ ቅድመ ኢህአዴግ ህወሓትን፤ ሻቢያን፤ ኦነግን አስተናግዳ ነበር። በማስተናገዷም ኢትዮጵያ የባህር በሯን አጥታለች። ባለፉት አመታት ደግሞ ኦነግን በከፍተኛ ደረጃ ደግፋለች፤ የዲፕሎማቲክ፤ የመሳሪያ፤ የገንዘብ፤ የስልጠና ድጋፎችን አበርክታለች። ባለውለታ ሸምታለች። ባለውለታ ውለታውን የመክፈል ግዴታ አለበት የሚል የግብጽ መንግሥት ስሌት ነው። ሌሎችም መንግሥታት የሚገቡባቸው ወንፊቶች ብዙ ናቸው። ቁም ነገሩ ጠንካራ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ወሳኝ መሆናቸውን ለመጠቆም ነው። እነዚህ ተቋማት ከማንኛውም ዘውግ የበላይነት በላይ መሆን አለባቸው።

በተጨማሪ፤ የኃይማኖት ጽንፈኝነት ስር እየሰደደ እንደሚሄድ የሚያመላክቱ ሁኔታዎች አሉ። እርግጥ ነው፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች የባንክ ሆነ ሌላ አገልግሎት በሰፊው አያገኙም። ይህ ክፍተት መሞላት አለበት፤ ለምሳሌ የባንክ ብድር አገልግሎት። ሁሉንም ዜጎች የሚያገልግልና በዝቅተኛ ወለድ ብድር የሚሰጥ ባንክ ኢትዮጵያ ለማቋቋም ትችላለች። አሁን ያሉትን ባንኮችም የብድር አሰጣጥ ሽፋናቸውን እንዲያስተካክሉና በዝቅተኛ ወለድ እንዲያበድሩ መንግሥት ድጎማና ዋስትና ሊሰጥ ይችላል። አድልዎ ለብሄራዊ አንድነት ጸር ነው። ማንኛውም አይነት አድልዎ በሕግ መከልከል አለበት።

የኢትዮጵያ መሰረታዊ፤ መዋቅራዊና ስርአታዊ ችግሮች ማንንም ኃይል በማባበል ሊፈቱ አይችሉም። በኢትዮጵያዊነት መንፈስ፤ በስልት፤ በብልሃት፤ በእቅድ፤ በድፍረትና በቆራጥነት ሊፈቱ ይችላሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገዢ መሆን ያለባቸው ለኢትዮጵያና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

ምሁራንና ልሂቃን በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ላይ ያለ አንዳች ፍርሃት፤ ወገንተኛነትና ቸልተኛነት ቁጭ ብለን መወያየት፤ መነጋገርና አማራጮችን መስጠት ብሄራዊ ግዴታችን ነው። ምሁራን እያሉ ይህች አገር የምሁራን ድሃ መሆን የለባትም።

ይህ አጭር የፖለቲካ ስእል ወደ ምርጫው ሃተታየ ይወስደኛል። ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወሳኝ ነው። ነጻነትና ፍትህ ከዳቦ በላይ ነው። ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣኑና የግል ኃብቱ ባለቤት እስካልሆነ ድረስ ሰላምና እርጋታ፤ አብሮነት፤ ዘላቂና ፍትሃዊ ልማት አይቻልም።

ከዚህ በፊት የታየው የምርጫ ክስተት ቅድመ ሁኔታዎች ካልተመቻቹ በስተቀር አስተማማኝ ውጤት እንደማያስገኝ አሳይቶናል። መድብለ ፓርቲዎች የተሳተፉበት፤ የፖሊሲ አማራጮች ለሕዝብ የቀረቡበት የዘጠና ሰባቱ ምርጫ በህወሓት/ኢህአዴግ ተሰረቀ። የቅንጅት መሪዎች ታሰሩ። ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ተጨፈጨፉ፤ ብዙ ሽህዎች ታሰሩ። በሚቀጥለው 2010 ምርጭ ኢህአዴግ መቶ በመቶ አሸነፈ። የአሁኑ ፓርላማ የዚያ ውጤት ነው። አንድ ፓርቲ ሃያ ስምንት አመት ገዛ። ወደፊትም የማያሸንፍበት ምክንያት የለም።

የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 54 የምክር ቤቱ አባላት በየአምስት ዓመቱ እንደሚመረጡ ደንግጓል። ጠ/ሚንስትሩም በየአምስት አመታት እንደሚመረጥ አንቀጽ 72 ያሳያል። በተመሳሳይ፤ የሕዝብ ቆጠራው በየአስር ዓመታት ይካሄዳል ይላል። የአገሪቱ ሁኔታ ያልተረጋጋ በመሆኑ፤ የሕዝብ ቆጠራው ተላልፏል። የምርጫ ቦርዱ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በማመዛዘንና የሕዝብ ቆጠራው መተላለፉን ከስሌቱ ጋር በማጣመር ምርጫው እንዲተላለፍ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። እስከዚያ ድረስ ግን፤ ጠ/ሚንስትሩ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ኢትዮጵያን ለመምራትና ውሳኔዎችን ስኬታማ ለማድረግ የማይችልበት ሁኔታ አይታየኝም።

 

በኔ እምነት፤ ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ እንዲሆን ከተፈልገ የገዢውን ፓርቲ መንግሥት የሚቆጣጠር ነጻና ጠንካራ ተቋም ያስፈልጋል። ምርጫ ትርጉም የሚኖረው ኢትዮጵያ ከገዢው ፓርቲ የተሻለ አማራጭ ስለሚያስፈልጋት ነው። “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ተቀጥላ ከሆኑ አማራጭ ሊኖር አይችልም።

ስለዚህ፤ የሚቀጥለው ምርጫ በአንድ ዓምት ውስጥ ይካሄድ ለሚሉት ወገኖች የሚከተሉትን አሉታዊ ሁኔታዎች አቀርባለሁ።

  1. የመጀመሪያውና ዋናው ትኩረት እርቅ፤ ሰላም፤ እርጋታና ሰብአዊ ደህንነት ማረጋገጥንና ማስተጋባትን ይጠይቃል።

 

  1. ከሶስት ሚሊየን በላይ የሚገመት ሕዝብ ተፈናቅሎ ምርጫ ማካሄድ ወቅታዊ አይደለም።

 

  1. ከአዲስ አበባና ከትግራይ ውጭ ሰላምና እርጋታ በሌለባት አገር ምርጫ ለማካሄድ ሁኔታው አመች አይደለም።

 

  1. የሕዝብ ቆጠራው ስለተላለፈ፤ በየትኛውም አካባቢ ማንና የት ለመምረጥ እንደሚችል በቅጡ አይታወቅም። የሕዝብ ቆጠራው ከምርጫው በፊት መካሄድ አለበት። የምርጫ ቦርድ ምክሩን ቢለግስበት መልካም ነው።

 

  1. በገዢው ፓርቲ ላይ ያለው የሕዝብ እምነት እየወረደ ሄዷል፤ ምርጫውን የሚጠራጠረው ሕዝብ በብዙ ሚሊየን ይቆጠራል። ዋናው ምክንያት የዜጎች ደህንነት እለመኖሩ ነው።

 

  1. ተራው ኢትዮጵያዊ ምርጫ የሚካሄደው የተለመደውን ቡድን ሥልጣን ላይ ለማቆየት ስለሚሆን ምርጫው ለይስሙላ እንጅ ለሕዝብ የፖለቲካ ስልጣን ስኬታማነት አይደለም ይላል።

 

  1. ምርጫውን ነጻና ፍትሃዊ ለማድረግ የተቋማት፤ በተለይ የምርጫ ቦርድ፣ የመከላከያ፤ የደህንነትና የፌደራል ፖሊስ ተቋማት ከማንኛውም ፓርቲ በላይ ነጻነትና ጠንካራነት እንዲኖራቸው በስራ ማሳየት ያስፈልጋል።

 

  1. ዲሞክራሳዊ ምርጫ ለማካሄድ ከተፈለገ ሁልጊዜም ኢህአዴግ ራሱን እንዲተካ መሆን የለበትም፤ ሕብረ ብሄር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ። ከስድሳ በላይ የሆኑት “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ተቀላቅለው ወደ ሶስትና አራት ሕብረ ብሄራዊ ፓርቲነት ቢሸጋገሩ ኢህአዴግን ለማሸነፍ ያላቸው እድል በብዙ እጆች ከፍ ይላል።

 

  1. የተሻሻለው የምርጫ ቦርድ የበላይ አካል ገዢው ፓርቲ ነው። ከማንኛውም ፓርቲ ቁጥጥር ነጻ የሆነ የምርጫ ቦርድ መመስረት ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል አንዱ መሆን አለበት።

 

  1. በአሁኑ ወቅት ከስድሳ በላይ የሚሆኑ “ተፎካካሪ” ፓርቲዎች ተመዝግበዋል ቢባልም፤ እነዚህ ፓርቲዎች የኢህአዴግ “ተቀጥላዎች” እንጅ በፖሊሲ ደረጃ ራእይ፤ ተልእኮና ፕሮግራም አውጥተው ራሳቸውን ከኢህአዴግ ለይተው ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጮችን ያቀርባሉ ብሎ ለመገመት የሚያስችል ሁኔታ የለም።

 

  1. የመመረጥ መብት እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ዐብይ የሚመራውን ኦዴፓን/ኢህአዴግን ለመምረጥ ከሆነ የሚካሄደው ምርጫ ካለፈው የሚሻልበት ሁኔታ አይታይም።

 

  1. ህወሓት “ምርጫው መተላለፍ የለበትም” እያለ ለማሳመን ይሞክራል። በአንድ በኩል ለፌደራሉ መንግሥት አልታዘዝም፤ ወንለጀኞችን አሳልፌ አልሰጥም እያለ በሌላ በኩል ምርጫው መካሄድ አለበት ሲል ምን “ድብቅ አጀንዳ” ይዞ ነው? ብሎ መጠየቅ አግባብ አለው። ታዳሚው የራሱን ግምገማ ያድርግ።

 

  1. ምርጫው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ይዘት ያለው ሆኖ፤ ተፎካካሪነት ያሳያል ብሎ ለመናገር የሚቻለው ፓርቲዎች አገር አቀፍ በሆነ ደረጃ በየትኛውም ቦታ ወይንም ክልል ቢሮ ለመክፈት፤ ያለ ምንም ፍርሃትና ጫና አቋማቸውን ለሕዝብ ለማቅረብ ሲችሉ ነው። ውድድር ማለት ይኼው ነው።

 

  1. ኢትዮጵያዊያን በዘውግና በቋንቋ ልዩነት ምክንያት ሰብአዊ መብታቸው እየተገፈፈ ከቀያቸው በሚፈናቀሉባት ኢትዮጵያ ሕብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች እንደልባቸው በየክልሉ ለመንቀሳቀስ የሚችሉበት ቅድመ- ሁኔታ ገና አልተፈጠረም፤ መፈጠር አለበት።

 

  1. የአንድነት “ኃይሉ” እርስ በእርሱ የተናከሰ፤ ደካማ፤ የተከፋፈለና የገንዘብ አቅም የሌለው ስለሆነ፤ ከኢህአዴግ ጋር አቻ ለአቻ ለመወዳደር አይችልም።

 

  1. “ተፊካካሪ ፓርቲ” የሚለውን ቃል እንደ ተራ ከመናገር ውጭ በመሬት ላይ የሚታየው ሃቅ በኢትዮጵያ ተፎካካሪ ፓርቲ ገና አልተመሰረተም።

 

  1. ኢትዮጵያ በዘውጎቿ ቁጥር ፓርዎች አያስፈልጓትም። በዘውግና በኃይማኖት የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት በሕግ መከልከል አለበት። የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በዚህ አስኳል ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ውይይት ማደረግ አለባቸው።

 

  1. ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ብሄራዊ ውይይትና መግባባት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚሉትን እሴቶች ሁሉም ፓርቲዎችና የህብረተሰብ አካላት ይጋራሉ ወይንስ አይጋሩም የሚለው ጥልቀትና ሃቀኝነት ያለው ውይይት ይጠይቃል።

 

  1. በአሁኑ ወቅት ሕወሓት ደካማ ነው ቢባልም፤ በፌደራል ደረጃ የተካው ህብረ ብሄር የሆነ ፓርቲ አይደለም፤ ኦዴፓ ነው። ኦነግ “ቦታ” ይዟል የሚሉ ታዛቢዎች አሉ። በዚህ ሁኔታ ጡንቻ ያለው ፓርቲ አገሪቱን ሊመራ ይችልላ ቢባል ምርጫው ቢካሄድ የሚመራው ማን እንደሚሆን አስቀድሞ ለማወቅ ይቻላል።

 

  1. ምርጫው የማያስተማምን ውጤት ያመጣል የሚለው ክፍል ፋይዳቢስ አይደለም። ሲካሄድ የቆየው ለውጥ በዐብይ መሪነት መሆኑ ባይካድም፤ ለውጡንና ጠ/ሚንስትሩን መለየት አስፈላጊ ነው።

 

  1. ለውጡ ሕዝባዊ እንጅ የአንድ ግለሰብ ወይንም የአንድ ቡድን አይደለም። ይህ ብዢታ መኖሩ ምርጫውን ይበክለዋል። ሆኖም፤ ዐብይ ከስልጣን ይውረድ የሚለው ብሂል ለኢትዮጵያ ዘላቂነት አደገኛ ስለሆነ በበኩሌ አልቀበለውም።

 

  1. ነገም እንደ ትላንቱ በትግራይ ክልል ህወሓት፤ በአማራው ክልል ዐዴፓ፤ በኦሮምያ ክልል ኦዴፓ ወዘተ እያለ ከተካሄደ ምርጫው የዜግነት ሳይሆን የዘውግ ይሆናል። ይህ ከሆነ የሚፈልገው እመርታዊ ለውጥ አይቻልም። ለምሳሌ፤ አንቀጽ 39 አይነካም። የዜጎች መፈናቀል ይቀጥላል። የመሬት ነጠቃው ይባባሳል። ወንጀለኞችን በሃላፊነት ለፍርድ ለማረብ ያለው ችግር ይቀጥላል። ኢትዮጵያዊነት ስኬታማ ሊሆን አይችልም።

 

  1. ድህረ ምርጫ የሚመረጠው ጠ/ሚንስትርና ሌሎች የበላዮች አሁንም ዝንባሌያቸው ዘውጋዊ ይሆናል። በአጠቃላይ ስመለከተው ምርጫው መተላለፍ አለበት።

ምርጫው እሰከሚካሄድ ድረስ ግን ተቋማትን ማጠምናከርና ዓብይን መደገፍ የህልውና ጥያቄ ሆኗል።

በተጨማሪ፤ ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ውይይት ተካሂዶ በአስኳል ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት። ውይይቱ ሁሉንም የዘውግ ተወካዮች፤ ፓርቲዎች፤ የማህበረሰብ ድርጅቶች፤ መንፈሳዊ ተቋማት፤ ሴቶችንና ወጣቶችን ማሳተፍ አለበት።

የፖለቲካ ልሂቃንን ብቻ ሰብስቦ ብሄራዊ መግባባት አይቻልም። ውይይቱ ሕዝባዊና ብሄራዊ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ይለምልም!

June 17, 2019

2019-06-26T19:41:14+00:00