ይድረስ ለአዴፓ፣ ለኦዴፓና ለደቡብ ህዝቦች ህብረት፡ /ኢህአደግ አመራሮች፡

እንደሚታወቀው የትግራይን ህዝብ እወክላለሁ የሚለው TPLF በኢህአደግ ጥምረት ውስጥ ከሚገባው በላይ መቀመጫዎችን በመያዝ 27 ዓመታት መግዛቱ እውን ነበር። 6 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብና የበሬ ግምባር የምታክል ቦታ የያዘው የትግራይ ክልል ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ከ25 ሚሊዪን ህዝብ በላይ ካላቸው ሶስቱ ድርጅቶች እኩል ድምጽና የውሳኔ መቀመጫዎችን ያለአግባብ ይዞ ቆይቷል። ይህ ከተደረጉት የዲሞክራሲ አፈናና ረገጣዎች በዋናነት የሚጠቀሰው አመራር ነው። በብዛታቸው፣ በቆዳ ስፋታቸውና ለሃገሪቱ በምታስገባው ምርት አንጻር እዚህ ግባ የማይባል አቅም ያላት ትግራይ ክፍለሃገር/ክልል ከአቅሟ በላይ መቀመጫዎችን በመያዝ  ከሶስቱ ድርጅቶች እኩል በኢህአደግ ውስጥ ድምጽና መቀመጫ ይገባታል ወይስ አይገባትም የሚለው ጥያቄ በአዋሳው ኮንፍረንስ ላይ መነሳት የሚገባው ወቅታዊ ጥያቄ ነው። ድርድሩ ዶ/ር አቢይ ይውረድ አይውረድ ሳይሆን ትግራይ ለህዝብ ብዛቷ መጠን የሚገባት መቀመጫ ይመደብላት ወደሚለው መቀየር አለበት ። ከሲዳማ እኩል የህዝብ ብዛት ያላት ትግራይ ከሲዳማ በላይ ድምጽና መቀመጫ መያዝ ዲሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ አይደለም።

  1. ኢህአደግ የድምጽ ውክልናውን በህዝብ ብዛት ማድረግ ይኖርበታል፤ ይህም ሌሎቹ 3 ክልሎች  የትግራይን አራት እጥፍ ህዝብ ብዛት ስላላቸው ተመጣጣኝ መቀመጫዎች (ማእከላዊ ኮሚቴውን ጨምሮ) ሊኖራቸው ይገባል።
  2. ምናልባት New Hampshire & Texas በአሜሪካን ሃገር እኩል ሴናተሮች አሏቸው ለምትሉ ፤ ምላሼ እኩል የህዝብ ተወካይ የኮንግረስ አባላት የላቸውም ይሆናል።
  3. ኢህአደግ ዲሞክራሲያዊ ነኝ የሚል ከሆነ ዲሞክራሲያዊ የሆነ የስልጣንና የውክልና መደላድል በድርጅቱ ውስጥ መኖር አለበት ።
  4. ትግራይ ክልል ከሱማሌ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከአፋርና ከጋምቤላ ክልል ጋር ተደምራ “የተቀሩት ክልልሎች ህብረት” ተብለው ከሶስቱ አጋር ድርጅቶች ጋር እኩል መሳተፍ ይኖርባቸዋል።
  5. ኢህአደግ እንደ አማራጭ ዲሚክራሲያዊ የሆነ አካሄድ እና የስልጣን ውክልና እንዲኖረው ከፈለገ አንድ ክልል የህዝብ ብዛቱ ከ6 ሚሊዮን የሚበልጥ ከሆነ ወደ ሁለት ወይም ሶስት ወይም አራት ቦታ መከፈልና ተመጣጣኝ መቀመጫ መያዝ ይኖርበታል ብሎ ውሳኔ ማሳለፍ ይጠበቅበታል። ይህ በጀርመን የፌዴራል ክልል አወቃቀር ውስጥ የተለመደ አሰራር ነው። በጀርመን አንድ የፌዴራል ክልል የህዝብ ብዛቱ ከ9 ሚሊዮን መብለጥ የለበትም። ይህም አሰራር አማራና ኦሮሞ ብዙ ህዝብ ስላላቸው የበላይነታቸውን ለረጅም ጊዜ በመያዝ የህዝብ ምርጫን ዋጋ ሊያሳጡት ይችላሉ የሚለውን ፍርሃት ያስወግዳል። በተጨማሪም ትልልቆቹ ክልልሎች ውስጥ አማራጭ ሃሳብና ርእዮት(IDEOLOGY) እንዲኖር በማድረግ የዲሞክራሲ አሰራሩን ሊያሳልጥ፣ ሊያፋጥንና መረጋጋትን በሃገሪቱ ውስጥ ለመፍጠር ይችላል።
  6. በዚህ አሰራር TPLF የማትስማማ ከሆነ ኢህአደግ ጥምረቱን አፍርሶ ወደ የህዝብ ተወካዮች ምርጫ በመሄድ ከምርጫ በኋላ በህዝብ ተወካዮች ብዛት ላይ የተመሰረተ አዲስ ጥምረትና መንግስት ለመመስረት ዝግጁ መሆን ያስፈልገዋል። ይህም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደ ሽግግር መንግስት ምስረታ ያስገባናል። 15 መቀመጫ አሸንፎ የሚመጣው ፓርቲ  60 መቀመጫ አሸንፎ ከሚመጣው ሌላ ፓርቲ ጋር እንዴትና ምን ያህል ስልጣን መያዝ እንደሚገባው ትምህርት ያገኛል።

ከትናንት ሲወዳደር በዶ/ር አቢይ ና ቲም ለማ ያገኘነው የዲሞክራሲ ድሎች የሚያመረቁ ቢሆኑም እንኳን ዛሬም ፍትሃዊ ያልሆኑ አሰራሮችን በተለይም ከዲሞክራሲ አሰራር ጋር አብረው የማይሄዱትን የህዝብ ውክልና መስፈርቶችን ማስተካከል ይገባናል። አዋሳ በሚኖረው የኢህአደግ ስብሰባ ላይ ዋና ጥያቄ ሆኖ መቅረብ ያለበት ጉዳይ ቢኖር ለትግራይ አቅሟን የሚመጥን የስልጣን ውክልና እንዲሰጣት የሚለው መሰረታዊ የዲሞክራሲ ስሌት መሆን ይኖርበታል።

ኮነ ፍሰሐ – Fseha@outlook.com

 

2018-10-02T23:01:27+00:00