ከኢትዮጵያ፤የውይይትና፤መፍትሔ፤መድረክ Ethiopian Dialogue Forum
የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ (EDF)አስተያየትና መግለጫ – December 29, 2019
ይህ መግለጫና አስተያየት የኢትዮጵያ የውይይትና የመፍትሄ መድረክ (Ethiopian Dialogue Forum – ኢዲኤፍ) አመራር አባላት ውይይት አድረገውበት እጅግ አሣሳቢ ሆኖ ስላገኘነው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲረዳው ከዚህ እንደሚከተለው አስተያየታችንን አቅርበናል። ህዝባችንም መንግስት ለታሪክ ማስተማርያ አዘጋጅቶ ያሰራጨውን ጽሁፉን በማንበብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና ጽሁፉ የረዥም ጊዜ ታሪካችንንና አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን እንድትረዱት በአክብሮት እንጠይቃለን።
ኢትዮጵያ ያላት ወሰን ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቧ መሬቷና አየሯ የረዥም ጊዜ አስገራሚ ታሪክ ያላት፤ በመላው ዓለም የታወቀች አገር ናት። ሰማይ ከነግሡ፣ ምድር ከነልብሱ መንክር ወመድምም የሚባልበት አገር መሆኗ አይካድም። በዓለም የምትታወቀው በጤናማ አየሯ፣ በታታሪ ሕዝቧ፣ በለምለም መሬቷ፣ በሰንሰለታማ ተራሮቿ፣ ከራሷ አልፈው የጐረቤቶቿን ሕይወት በሚንከባከቡ ዥረታዥረቶቿና ወንዛወንዞቿም ብቻ አይደለም። በረጅምና በአስደናቂ ታሪኳም ጭምር ነው። ይሁንና የዛሬ ዕድለኞች ነዋሪዎቿ በዚህ ሁሉ እንደመኩራት፣ አገራቸውን ይበልጥ እንደማሳደግ፣ በዘመኑ ሥልጣኔ ወደፊት በመግፋት ታሪካዊ ታላቅነታቸውን ተግተው እንደመጠበቅ ፋንታ፣ የሚታዩት ታሪኳን በመበረዝ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ሲነታረኩ ዓለም ጥሏቸው እየገሠገሠ፣ እነሱም አርጅተውና ጃጅተው ወደ ማይመለሱበት አገር ሲጓዙ ነው።
የታሪክ ትርጉሙ ምንድን ነው?
ታሪክ ማለት ያለፈው የሰው ልጅ ተግባር ጥናት ነው። እዚህ ላይ ሁለት ነገር መለየት ይኖርበታል። በአንድ በኩል “ያለፈው የሰው ልጅ ተግባር” ሲሆን በሌላው በኩል ደግሞ “ጥናት” የሚለው ነው። ብዙ ጊዜ “ታሪክ”ና “ያለፈው የሰው ልጅ ተግባር” ሲደባለቁ ይታያሉ። ያለፈው ስንል የሰው ልጅ ተግባር ማለትም ከኛ በፊት ድሮ የነበረው ሕዝብና ማኅበረሰብ የኖሩበትንና በወቅቱም የተፈጸሙ ክሥተቶችን ያመለክታል። ይኸንን ለመመርመር፣ ለማጥናትና ለማብራራት የምናደርገው ጥረትና ሙከራ ታሪክ እንለዋለን። ያለፈው ስንል ደጉንም መጥፎውንም፣ ስኬቶችንና ውድቀቶችን ሁሉ ያካትታል። ይኸ ሁኔታ ከሰው ቊጥጥር ውጭ የሆነ፣ በምንም መልክ የማይቀየር፣ የማይለወጥ ዘለዓለማዊ ሐቅ ነው።
ታሪክ በተቃራኒው በየጊዜው ይቀያየራል። እያንዳንዱ ትውልድ፣ ግለሰብና ቡድን ይኸንን ሐቅ የሚያይበት መነጽር እንደጊዜውና እንደ ቦታው ይለዋወጣል። ትርጒሙ ይቀየር እንጂ ያለፈው መነገር ያለበት፤ ተበርዞና ተደልዞ ሳይሆን እንዳለ ነው። ከ”ያለፈው” ውስጥ ትርጒማቸው በምንም መልክ የማይቀይሩ አንዳንድ ሐቆች አሉ። ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያውያን፤ ተመካክረውና ተባብረው በአድዋ ጣሊያኖችን አሸንፈዋል የሚለውን ሐቅ የለም “አላሸነፉም” የሚል የማንኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን አስተያየት አለአንዳች ጥርጥር ውሸት ነው። ክርክርና የአስተያየት ልዩነት የሚመነጨው ድሉ እንዴት ተገኘ፤ ማንስ ምን ሚና ተጫወተና ወዘተ. በሚሉ ጉዳዮች ላይ እንደጊዜው፤ እንደግለሰቡና እንደ ስብስቡ የሚሰጠው ፍርድና ትርጒም ይቀያየራል። ማንኛውም አስተያየት ዋጋና ጥቅም የሚኖረው ዝም ብሎ በጭፍኑ “የለም እንደዚህ አይደለም” በማለት ሳይሆን በተጨባኝ አስተማማኝነቱ በተረጋገጠ ማስረጃ ሲደገፍ ብቻ ነው። ታሪክ ከልበወለድ፣ ከግጥምና ከሌሎችም የማኅበረሰብ ትምህርት፣ ከድርሰትና ከተረት ከመሳሰሉት መስኮች የሚለየውም ማንኛውንም አስተያየት አለማስረጃ የማይቀበል በመሆኑ ነው። የማስረጃ ዐይነት ድሮ በቅርጽ ወይንም በግንብና በቀለም የተወሰነ ሲሆን፣ የታሪክም ቢያንስ እስከ ዐሥራ ዘጠነኛው መቶ መጀመርያ ዓመታት ድረስ ዋናው ትኩረቱ በየጊዜው በሚያጋጥሙ መቅሠፍቶችና ጦርነቶች፣ ጦርነቱንም በሚመሩ ሰዎች ማለትም በነገሥታቱና በጦር መኳንቶቻቸችው ላይ ነበር። በሃያኛው መቶ ዘመነ-ምሕረት ግን የታሪክ ምንጮች እንደቤቶች፣ አልባሳት፣ ተንቀሳቃሽ ሥዕሎች፣ የአየር ፎቶዎች፣ የዛፎች ቀለበቶች፣ አሮጌ ሳንቲሞች የመሳሰሉትን እስከመጨመር ሰፍቷል። በጽሑፍ የተላለፈ ነገር ስለሌላቸው፣ አውሮፓዊያን እስካገኟቸው ድረስ ታሪከ አልባ ተብለው ይገመቱ የነበሩ የተለያዩ የዓለም ማኅበረሰቦች፣ አፈታሪካቸውን ከሥነፍርስራሽ ጥናት [አርኬኦሎጂ] ጋር በተራቀቀ መንገድ በመመርመር፣ የሥልጣኔአቸውን ጠባይ ለመመዝገብ ተችሏል።
የዚህ መግለጫ ዋና ትኩረት የሆነው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር (Ethiopian Ministry of science and Higher Education) ያወጣው የታሪክ ማስተማርያ ካሪኩለም ታሪክን እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ ትምህርት በማሻሻል ስም፣ የወቅቱን የፖሊቲካ የበላይነት ለማራመድ በሚያስተጋባ ዘዴና ይዘት የዩኒቬርሲቲዎችን የአካዳሚክ ነፃነት ሊገፍና በእጅ አዙር ሊቈጣጠራቸው እየሞከረ ያለ የፖሊቲካ ግብ በመሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን የተሳሳተና ታሪክን የሚበርዝ ሂደት እንዲከላከለው አደራ እንላለልን። ለትኩረት ይረዳ ዘንድ በረቂቁ ውስጥ ከሚታዩት ከፍተኛ ስሕተቶች ውስጥ የሚከተሉትን እናቀርባለን።
አንደኛ፣ የረቂቁ ታሪክን ለመቀየር ምክንያት አድርጎ የተነሳበት ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ታሪክ ብለን እስከዛሬ እንጠቀምባቸው የነበረውን የአንዳንድ ብሔሮችን “ገድል” ብቻ የሚዘክር እንጂ፣ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ታሪክ፣ በተለይም የኦሮሞዎችን ታሪክ የማያወሳና አግላይ “ታሪካዊ መረጃ” ነው ብሎ በመፈረጅና የሚታመን አይደለም የሚል አቋም በመያዝ ነው። ከዚህ የተሳሳተ አቋም ላይ በመነሳት ምንም ዐይነት መረጃ የሌላቸውን የአንዳንድ ብሔረሰቦች ፈጠራዎችንና ልበወለዶችን አላንዳች ምርምር ተማሪው እንደ እውነተኛ ታሪክ እንዲቀበለው በሰፊው አትቷል።
ሁለተኛ፣ በታሪክ ሥርዓተ ትምህርት አመካኝቶ መንግሥት በወቅቱ እያራመደው ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት መደበኛነቱንን ሕጋዊ መሠረቱን በዘለቄታ ሊያረጋግጥ እየሞከረ ነው። ይህም ማለት የጠባብ ብሔርተኞችን ዓላማ ለማሳካትና በሐሰት ታሪክ በመመሥረት የኢትዮጵያ ሕዝብ በጐሣ ተከልሎና ተከፋፍሎ እንዲኖር ማረጋገጥን እንደትልቅ ተልእኮው አድርጎ ይዞታል። ሥርዐተ-ትምህርቱም የሚያንፀባርቀው አሁን ያለው ክልል ታሪካዊ እንጂ የኢሕአዴግ ፈጠራ እንዳልሆነና በዚሁም መቀጠል ተገቢ እንደሆነ ሊያሳይ ይጥራል።
ሶስተኛ፣ ረቂቁ የኢትዮጵያን ዓለም ያደነቀውንና የተቀበለውን ታሪካዊ አንድነትና ሉዐላዊነት መልሶ የማቋቋም ታሪክን እንደወረራ ይቈጥራል፤ አፄ ምኒልክ በአርሲ፣ በሐረርና በወላይታ ያካሄዱትን የአገር አንድነትን የግንባታ እንቅስቃሴ በተንሻፈፈና መረጃ በሌለው እይታው በወረራ መነጽር ከማየት ዐልፎ፣ ጡት ቈረጡ፤ አባለዘር ጎመዱ ሲል በማስረጃ ያልተደገፈ ፈጠራ ያካትታል። ይህ ሁኔታ ጭፍን ጥላቻን የሚያንጸባርቅ እንጅ እውነተኛውን የኢትዮጵያን ታሪክ ለተከታታይ ትውልድ የሚያስተምር አይደለም።
አራተኛ፣ በርካታ የሆኑትን የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች በወረራና በአስከፊ ጦርነት፣ በማፈናቀል፣ በመግደል፣ በመጨፍጨፍና ከፍተኛ ጥቃት በማድረስ የተስፋፋውን የኦሮሞውን ብሔረሰብ ታሪክ ከሚገባው በላይ በማስረጃ ባልተደገፈ ትርክት (False and misleading narratives) ተጠቅሞ ያጀገንናል። አልፎም የመስፋፋት ሂደቱ በሰላምና በፍቅር እንደተደረገ አድርጎ ያቀርባል።
በኛ ተቋም ጥናትና ምርምር መሰረት፤ ልንጠቁመው የምንፈልገው አስኳሉ ጉዳይ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያየ ሙያና መስክ የታወቁ ምሁራንና ባለሞያዎች ጉባኤ ተጠርቶና ተሰብስቦ ጥናት ይደረግ የሚል አገራዊና ኢትዮጵያያዊ ጥሪ ሲሆን፤ የሚሰበሰቡትም ምሁራንና ባለሞዎች ስራቸውን ሊሰሩ የሚችሉት አላንዳች የመንግሥት ጣልቃገብነት፣ አላንዳች የፖለቲካ ግፊትና ያለምንም የህብረተሰብ አካል ተፅእኖ መሆኑን እናሰምርበታለን።
ይህንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ ለተከታታይ ትውልድ የሚጠቅም ጥናትና ምርምር በገለልተኛነትና በሃቀኛነት ለማቅረብ የሚቻለው በገንዘብና በስራ ወይንም በፖለቲካ ፍጆት ጥቅሞች ሳይሆን፤ ዕውቀትን ለመፈለግ፣ ለማስተማር፣ ሃቀኛውን የኢትዮጵያን ረዢም ታሪክ ለመጠበቅና ለማሰራጨት መሆን ይገባዋል። የሥርዓተ ትምህርቱ ባለቤቶች ዩኒቬርሲቲዎች በመሆናቸው ስርዓተ ትምህርቱን የሚያዝጋጁና የሚቀይሡ፣ ተማሪው ምንና እንዴት መማር እንደሚገባው መወሰን የነርሱ የሞያ ድርሻቸው ነው።
በመጨረሻ፤ ኢዲኤፍ፣ መንግሥትም ሆነ የፖሊቲካ፤ ሃይሎች የኢትዮጵያን ታሪክ ለፖለቲካ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ፣ ለስልጣን ዘመናቸው ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ፣ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት በትምህርት ላይ ያለውን የሚዘገንን ተንኮል፤ ጫናና ተቀባይነት የሌለው ፖሊሲ ይቃወማል።
ይህ ፖሊሲ ስኬታማ ከሆነ በአገራችን በኢትዮጵያና በተከታታይ ትውልድ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ውጤት ከፍተኛና አደገኛ ነው። ያለውን አለመተማመንና አለመረጋጋት ያባብሰዋል።
የኢትዮጵያ የፌደራል ባለሥልጣናት ታሪካዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ምክራችን እንገልጻለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
የኢትዮጵያ፤የውይይትና፤መፍትሔ፤መድረክ
Ethiopian Dialogue Forum (EDF)
9900 Greenbelt RD. E#343 – Lanham, MD 20706
Tel. +1-202-641-5517 – www.Ethiopiandialogueforum.org