8/22/19: Washington DC:- የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ለምን መቀየር እንዳለበት ተጨባጭ ምክንያቶችን ከመሰንዘራችን በፊት የሕገ-መንግሥትን ትርጉምና ዋና ዓላማ ምን እንደሆነ ባጭሩ መመልከቱ ለግንዛቤ ይረዳል::
ሕገ-መንግሥት ማለት የአንድ አገር የሕጎች ሁሉ እናት ወይም የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው:: ዋና ዓላማውም በአንድ መልክአ-ምድር በአንድ መንግሥታዊ አስተዳደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሰላማቸው እንዲጠበቅ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውና ነፃነታቸው እንዲረጋገጥ፣ የጋራ ደኅንነታቸው እንዳይናጋ፣ ተፈጥሮአዊ የሆነው ሀሳብን የመግለጽ የፈለጉትን ሃይማኖት የማምለክ ነፃነትና መብቶች ተከባሪ እንዲሆኑ፣ የሚደነግግ የአገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው:: ባጭሩ ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ዕኩልነት እና ወንድማማችነት የተሰኙት መርሆዎችን ያካተተ የዜጎችን መብቶችና ነፃነቶች፣ የመንግሥትን ኃላፊነትና ግዴታዎች፣ የመንግሥቱን አደረጃጀት ዓይነትና ቅርጽ፣ አገሪቱና ሕዝቡ የሚመሩበትን የዕድገት ፈለግ፣ የሚከተሉትን የኢኮኖሚ ሥርዓትና የዓለም አመለካከት የሚወስን፣ በምላተ ሕዝቡ ይሁንታ የሚጸድቅ፣ በዜጎችና በመንግሥት መካከል ለሚኖር ግንኙነት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው::
እነዚህን ጉዳዮች አካቶ ከ250 ዓመታት በላይ የዘለቀውና የዲሞክራሲ አስተዳደር ምሳሌ በመሆን የሚጠቀሰው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ የሕገ-መንግሥት ዓላማ ምን እንደሆነ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል:: ”የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች ፌደራላዊ መስተዳድር ሕገ-መንግሥት ዓላማዎች ፍትሕን ማስፈን፣ ውስጣዊ ሰላምንና የጋራ መከላከያን ማረጋገጥ፣ አጠቃላይ ማኅበራዊ ዋስትናን ማስፋፋት እና የተፈጥሮ ሥጦታ የሆኑትን ነፃነቶችና መብቶችን ለራሳችንና ለሁላችን ብልጽግና ማስጠበቅ” እንደሆነ ይገልጻል::
በተመሳሳይ ሁኔታ የሕንድ ሕገ-መንግሥት ዓላማዎች የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍትሕ መረጋገጥ፣ የሀሳብ የእምነት እና የሃይማኖት ነፃነት መከበርና የሁኔታዎች (opportunity) እና ደረጃዎች (status) ዕኩልነት መረጋገጥ ዓይነተኛ ዓላማው እንደሆነ ያስረዳል::
ከነዚህ አጠቃላይ የሕገ-መንግሥት ትርጉምና ዓላማ ስንነሳ ሕገ-መንግሥት በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሁለቱ አካሎች ግንኙነት ግዴታና ኃላፊነቶችን የያዘ ውል ወይም ማኅበራዊ ስምምነት ነው:: ስምምነቱም ቀጣይና ዘላቂ የሚሆነውም ሁለቱም አካሎች ሰነዱ ለሰጣቸው ኃላፊነቶችና ግዴታዎች ሳያዛንፉ በሥራ ላይ ሲያውሉ ነው:: በታሪክ ተደጋግሞ እንደታየው ሕዝብ ቃሉን አክባሪ ግዴታውን ተወጭ ሲሆን መንግሥታት በተለይም አምባገነን የሆኑ የገቡትን ውል ሲያከብሩ አይታዩም:: በመሆኑም በሕገ-መንግሥቱ የተገለጹትን መብቶችና ነፃነቶችን የሚገፈው መንግሥት(state) ወይም መስተዳድር (government) እንደሆነ ይታወቃል:: መንግሥት የዜጎችን መብቶችና ነፃነቶች የሚገፍባቸው ምክንያቶች የተለያዩ እንደሆኑ ቢታወቅም ዋና ዋና ምክንያቶቹ ግን የሚከተሉት ናቸው::
- አንደኛ ሕዝብ ያልመከረባቸውን ያልተስማማባቸውን እና ያላመነባቸውን ሕጎች በልዩ ልዩ ጫና የሕገ መንግሥቱ አካሎች ማድረግ::
- ሁለተኛ በአስፈጻሚ አካሉ ጫና እና ተጽዕኖ ሕገ-መንግሥታዊ ባልሆነና የሕግን ሂደት ባልተከተለ መንገድ በሕግ ስም በዜጎች መብትና ነፃነቶች ላይ ጫና ሲፈጠር::
- ሦስተኛ ከማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር ተያይዞ ሕገ-መንግሥቱ አልሻሻል ሲል እና የዜጎችን ፍላጎቶች ማሙዋላት ሲሳነው:: ይህም በመሆኑ ሕገ-መንግሥቶች የሰላም የነፃነት የዕኩልነትና የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይወት መሠረት መሆናቸው ይቀርና የብጥብጥና የእገዛለሁ አልገዛም ምንጭ በመሆን የአገር እና የሕዝብ ሰላም ጠንቅ ይሆናሉ::
በዛሬው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የችግሮች ሁሉ ምንጭ ይኸው ሕገ-መንግሥት የሚባለው ነው:: ላለፉት 28 ዓመታት ሕዝቡ ምትክ የለሽ ሕይወቱን መስዋዕት በማድረግ የአንድነቱ የሰላሙ የጥቅሙ የመብቶቹና የነፃነቶቹ ሁሉ ፀር የሆነው ሕገ-መንግሥት ይለወጥ ወይም ይሻሻል እያለ እየጮኸ ያለው ሕገ-መንግሥቱ ከዜጎች መብቶች ነፃነቶች ጥቅሞችና ፍላጎቶች ተፃራሪ በመቆሙ ነው::
እንደ “አማራ ህልውና ለኢትዮጵያ አንድነት” ድርጅት እምነት ሕገ-መንግሥቱ ይቀየር ወይም ይሻሻል የምንለው በሚከተሉት ተጨባጭ ምክንያቶች ነው::
- ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀ ሲዘጋጅ እና እንዲጸድቅ ሲደረግ ከሚሊዮን በላይ የሆኑትን ስለሕገ-መንግሥት ምንነት ሠፊ ዕውቀት ያላቸውን የተካበተ ልምድና የአገር ምንነት በቅጡ የሚያውቁትን ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት መጠበቅ ከፍተኛ መሥዋዕትነት የከፈሉትን (ሀ) ከሰባት መቶ ሺህ/700,000/ በላይ የሆኑትን የመከላከያ ሠራዊት አባሎችን (ለ) በሽዎች የሚቆጠሩትን የፖሊስ ሠራዊት አባላትን (ሐ) ከአንድ ሚሊዮን /1,000,000/ በላይ የሆኑ የኢሠፓ አባላትን (መ) በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ በአገሪቱ የሚገኙ የከተማ ቀበሌ ማኅበራት ከቀበሌ እስከ አጠቃላይ የከተሞች ማኅበራት ተመራጭ የነበሩትን (ሠ)በመላ አገሪቱ በሚገኙ ከገበሬ ቀበሌ ማኅበር እስከ አገር አቀፍ የተደራጁ ማኅበራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመራጮችን (ረ) በገጠርና በከተማ ከቀበሌ እስከ አገር አቀፍ የተደራጁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የወጣትና የሴቶች ማኅበራትን አመራሮችን (ሰ) ከመሠረታዊ ማኅበር እስከ አገር አቀፍ የተደራጁ የሠራተኛ ማኅበር ተመራጬችን (ሸ) ቁጥራቸው በአሥር ሽዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱን የደኅንነት ሠራተኞች ወዘተ በፖለቲካ አቁዋማቸው ብቻ ያለሕግ ሂደት በሕገመንግሥቱ ቀረፃና ጸደቃ ሂደት ላይ በፖለቲካ ውሣኔ ድምፅ እንዳይሰጡ ተደርገዋል:: በመሆኑም እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች እንዳይሳተፉ በመደረጉ ሕገ-መንግሥቱ በዜጎች መብትና ጥቅም ላይ የቆመ እንጂ የቆመላቸው ባለመሆኑ የነዚህ ዜጎች ድምፅ ሊሰማ ይገባል:: ይህም ሕገ-መንግሥቱ እንዲሻሻል ግድ ያደርገዋል:: ሕገ-መንግሥቱ ሲጀመር ዜጎችን አግላይና ከፋፋይ በመሆኑ የአገሪቱ ሰላምና አንድነት ፀር ሆኖ የቆመ ስለሆነ እውነተኛ ሰላምና አንድነት በነበረ መልኩ እንዲቀጥል ለማስቻል የጥላቻና የመለያየት ግንብ የሆነው ይህ ሕገ-መንግሥት መለወጥ አለበት::
- ሕገ-መንግሥቱ የግለሰብን ነፃነት የሚፃረር ከመሆኑም በላይ ለግለሰብ ዜጎች መብት አይሰጥም:: መብት የሚሰጠው “ለብሔር/ ብሔረሰቦች/ ሕዝቦች” ለሚላቸው ትርጉማቸውና ማንነታቸው በግልጽ ለማይታወቁ አካላት ነው:: በሌላ በኩል ቁጥራቸው ከአንዳንድ ብሔረሰቦች እና ብሔሮች እጅግ የሚበልጥ መጠን ላላቸው ከሁለት እና ከዚያም በላይ ብሔር/ብሔረሰቦች/ሕዝቦች ለሚወለዱ ሰዎች የዜግነት መብታቸውን በመግፈፍ የአባት ወይም የእናት ማንነታቸውን ተገደው እንዲመርጡ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲጠፋ ያደረገ በመሆኑ እነዚህ ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ዜጎችን መብትና ነፃነት ለማስከበር ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ግድ ይለዋል::
- ሕገ-መንግሥቱ ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኩዋ የገነባቻቸውን የወል እሴቶችና የታሪክ ጉዞ በመካድ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ጸንተው የቆዩትን መልካም ግንኙነቶች “የተዛቡ” ናቸው:: ያዛባውም ዐማራ ነው በማለት ዐማራው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ዓለም አቀፍ ወንጀል ሰለባ እንዲሆን በመሣሪያነት ያገለገለ በመሆኑ የነባሩ ኢትዮጵያዊነት የወልና የአብሮነት የግንኙነት እሴቶች የሆኑት ተገቢ ቦታቸውን እንዲይዙ ሕገ-መንግሥቱ መለወጥ ወይም መሻሻል ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው::
- በኢትዮጵያ ካሉት ነገዶች በቁጥሩ ከፍተኛ የሆነው የዐማራ ነገድ በጠላትነት ተፈርጆ በሕገ-መንግሥቱ ማርቀቅና ማጽደቅ ሂደት እንዲወከል አልተደረገም:: በመሆኑም በሕገ-መንግሥቱ የዐማራውን ጥቅምና መብት ያላካተተ ስለሆነ ሕገ መንግሥቱ መለወጥ አለበት::
- ሕገ-መንግሥቱ ልዩነትን የሚያራባ መነጣጠልን የሚሰብክ በመሆኑ የአብሮነት የሰላም እና የልማት ፀር ነው:: በመሆኑም ለኢትዮጵያ አንድነት ጠንቅ ነው:: የልማትና የዕድገት ማነቆ ነው:: ይህም በመሆኑ ዛሬ አገሪቱ ለገባችበት ሁለንተናዊ ችግር ምክንያቱ ሕገ-መንግሥቱ ስለሆነ ይህን መለወጥ ግዴታ ነው::
- ሕገ-መንግሥቱ የአገሪቱን ረጅም የአገርና የመንግሥትነት ታሪክ የሕዝቡን ውስብስብና ጥብቅ መስተጋብር ክዶ እና የነበረውን ንዶ በአዲስ ማንነት ላይ ለመመሥረት ያለመ በመሆኑ ይህም የሕዝቡ ማኅበራዊ ሰላም ዕድገትና ብልፅግና ፀር በመሆኑ የሕገ-መንግሥቱን መቀየር ግድ ያደርገዋል::
- የአገሪቱን ዓለምአቀፋዊ ድንበር ዓለም በሚያውቃቸው ቁዋሚ ምልክቶች ሳይሆን ጠፊ እና ዕውቅና በሌላቸው የብሔር/ብሔረሰቦች/ሕዝቦች ክልል ድንበር ነው ማለቱ የአገሪቱን የምድርና የአየር ክልል በቁዋሚነት ለማስጠበቅ የማያስችል ስለሆነ ሕገ-መንግሥቱ ዳር ድንበሩ በቁዋሚ ምልክቶች መገለጽ ስላለበት ይህን ዕውን ለማድረግ የሕገ-መንግሥቱ መለወጥ የግድ አስፈላጊ ነው::
- ሕገመንግሥቱ በልዩነት ላይ የተመሠረተና ልዩነትን የሚያራባ ከመሆን ዘሎ የአገሪቱን የመንግሥት አደረጃጀት በቁዋንቁዋ ልዩነት ላይ ያዋቀረ ነው:: ይህም ለዘላቂ ሰላም ተከታታይ ዕድገት እና አብሮነትን አያጎናጽፍም:: ሰላምና ተከታታይ ዕድገትና አብሮነት ከሌሉ ኢትዮጵያ እንደአገር መቀጠል አትችልም:: እንደአገር እንድትቀጥል በዚህ ከፋፋይ ሕገ-መንግሥት መሣሪያነት የተደራጀው የፌደራል መንግሥት አሀዶች አደረጃጀት መለወጥ አለበት:: ይህም የሕገ-መንግሥቱን መለወጥ ግድ ያደርገዋል::
- ከፌደራሉ ሕገ-መንግሥት የመነጩት የየክልሉ ሕገ-መንግሥቶች የክልሉን ባለቤትነት የሚሰጡት ክልሎቹ ለተሰየሙባቸው ነገዶች ነው:: ለምሳሌ የትግራይ ክልል ባለቤቱ ትግሬ ነው:: የኦሮሚያ ክልል ባለባቱ ኦሮሞ ነው:: የአፋር ክልል ባለቤቱ አፋር ነው:: በነዚህ ክልሎች የሚኖሩ የሌሎች ነገድ አባሎች የክልሉ ባለቤትነት የላቸውም:: የነዚያ ክልሎች ባለቤቶች ሁለተኛ ዜጎች ናቸው:: የክልሉ ባለሥልጣኖች ባሻቸው ጊዜ መጤዎች ብለው ሊያባርሩዋቸው ይችላሉ:: ዐማራው በተለያዩ ክልሎች ለዘመናት ከኖረበት አካባቢዎች የተባረረው ሕገ-መንግሥቱ የባለቤትነት ዋስትና የከለከለው በመሆኑ ነው:: በሌላ በኩል ዐማራ የተባለው ነገድ በእርሱ ስም የተከለለው ክልል ባለቤት አይደለም:: ይህም በመሆኑ ዐማራው ዐማራው በስሙ በተሰየመው ክልልም ሆነ ከክልሉ ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ የግዛት አካል የባለቤትነት መብት የለውም:: ለዚህም ነው ሕገ-መንግሥቱ ፀረ ዐማራ ነው የሚባለው:: ይህ በቁጥሩ ከፍተኛ ከሚባሉት ነገዶች ግንባር ቀደም የሆነን ነገድ የአገር ባለቤትነት የነፈገ ሕገ-መንግሥት ባለበት መልኩ ይቀጥል ማለት በዐማራው ላይ የዘር ጥፋት ወንጀል ማወጅ ነው:: ይህ እንዲሆን ደግሞ ዐማራው አይፈቅድም:: በመሆኑም ሕገመንግሥቱ መሻሻል አለበት::
- ሕገ-መንግሥቱ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት ሰነድ ሆኖ በዘላቂነት እንዲያገለግል ተደርጎ የተቃኘ አይደለም:: ዘላቂ ሆኖ እንዲያገለግል ቢፈለግ ኖሮ በአገሪቱ የሚገኙ ብዙኃን ሰዎች ቀርቶ ግለሰቦች በሂደቱ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ይደረግ ነበር:: የሆነው ተቃራኒው ነው:: ሕገ-መንግሥቱ የትሕነግ/ወያኔ እና የኦነግ ኢትዮጵያን የማፈራረሻ ፕርግራም ነው:: የፖለቲካ ድርጅቶች ፕሮግራም በምንም ተዓምር የአገር ሕገ-መንግሥት ሊሆን አይችልም:: በመሆኑም ሕዝባችን በሁለት ፀረ ኢትዮጵያ ቡድኖች ፕሮግራም ሊገዛ አይገባምና መለወጥ ወይም መሻሻል አለበት::
- ሕገ-መንግሥቱ የተቃኘው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የዓለም አመለካከት ነው:: ይህ አመለካከት ደግሞ ለገቢያ መር ኢኮኖሚና ለነፃ ውድድር ሥርዓት ተቃራኒ ከመሆኑም በላይ የዲሞክራሲ ዋልታ ለሆነው የሕዝብ ተሳትፎ በሩ ዝግ የሆነ ስለሆነ ለነፃ ገበያና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ በሆነው የሊበራል የዓለም አመለካከት መተካት አለበት:: ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ሕገ-መንግሥቱ መለወጥ ወይም መሻሻልን ይጠይቃል::
- ሕገ-መንግሥቱ ከጥንስሱ እስከ ድምዳሜው ሕዝብ የመከረበትና የተወያየበት አይደለም:: በመሆኑም ሕገ-መንግሥቱ በሕዝብ ላይ የተጫነ በመሆኑ የኔ ብሎ የተቀበለው አይደለም:: ይህ ሕገ-መንግሥት ምላተ-ሕዝቡ ሊመክርበትና ሊስማማበት ቀርቶ ሕገ-መንግሥቱ እንዲረቀቅና እንዲጸድቅ ብሎም በፊርማቸው ያጸደቁት ዶር ነጋሦ ጊዳዳን ጨምሮ በማርቀቅ ሂደቱ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው አቶ ክፍሌ ወዳጆና ዶር ኃይሌ ወልደሚካኤል ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የማይበጅ ከፋፋይ እንደሆነ በሂደቱም ሆነ በፍጻሜው ተናግረዋል:: ስለሆነም ሕገ-መንግሥቱ የሕዝቡን አንድነት ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ተከታታይ ዕድገትና ብልጽግና የሚያረጋግጥ ስላልሆነ መለወጥ ወይም መሻሻል አለበት::
- ሕገ-መንግሥት ሰላም፣ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ተከታታይ ዕድገትና ብልጽግና እንዲሰፍን ቁልፍ መሣሪያ እንደሆነ ይታመናል:: የዚህም መሣሪያ ማስፈጸሚያው የመንግሥት ቢሮክራሲ ቁጥጥርና ሚዛን(Check and Balance) መኖር ነው:: ይህም ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጉዋሚና አስፈጻሚ የሚባሉት ታላላቅ አካሎች ሕገ-መንግሥቱ በሚደነግገው መሠረት ሥራዎች መከናዎናቸውን ለማረጋገጥ አንዱ ሌላውን ይቆጣጠራል:: ይጠብቃል:: ዝንፈት ሲከሰትም አስቸኩዋይ እርምት እንዲወሰድ አንዱ ሌላውን ያስገዳል:: በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እነዚህ አካሎች በራሳቸው ነፃ ሆነው የማይንቀሳቀሱ በመሆኑ ይህ አንዱ አካል ሌላውን የመቆጣጠርና ሚዛን የመጠበቅ ሁኔታ የለም:: የአስፈጻሚ አካሉ ያሻውን በማድረግ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን መብቶችና ነፃነቶች ይገፋል:: ይገድባል:: ይህም በመሆኑ ሕግና ሕጋዊነት ከሁሉም በላይ በሕግ የበላይነት ምትክ የግለሰቦች ወይም የድርጅቶች የበላይነት ሰፍኑዋል:: ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ፀረ ዲሞክራሲ አሰራርና አስተሳሰብ ስለሆነ የሕገ መንግሥቱን መቀየር ወይም መሻሻል ግድ ያደርገዋል::
- የሕገ መንግሥት ጉዳዮች የትርጉም ችግር ሲነሳ እንዲተረጉም ሥልጣን የሰጠው በብሔር/ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ኮታ ላይ ተመሥርቶ ለተዋቀረ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው:: ይህ አካል የሕግ ዕውቀቱና ልምዱ ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ ከመታወቁም በላይ ተመራጮቹ በፖለቲካ ድርጅት አባልነታቸውና በሚያራምዱት አመለካከት ታጭተው የተመደቡ እንጂ ስለሕግና ሕጋዊነት በቂ ዕውቀት አላቸው ተብለው የተሰየሙ አለመሆናቸው ግልጽ ነው:: በሌላ በኩልም የሕግ ዕውቀት አላቸው ወይም በሙያተኞች ያሠራሉ ከተባለም ሕግ የመተርጎም ኃላፊነት ሊሰጠው የሚገባው የፍርድ ሥርዓቱ አካል ወይም የተለየ ኮሚሽን እንጂ ይህ አካል ሊሆን አይገባውምና ለዚህም ሲባል ሕገ- መንግሥቱ መሻሻል ወይም መለወጥ አለበት እንላለን!
- የአሁኑ ሕገ መንግሥት የአገሪቱን ሥልጣን የሚቆጣጠረው በምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ወይም ያገኙት ድርጅቶች በጥምረት እንደሆነ ይታወቃል:: ይህ በድርጅት ስም ባንድ ቀበሌ የተመረጠ ሰው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሁን ማለት ለሕዝቡም ሆነ ለተመራጩ የሞራል ልዕልናን የማያጎናጽፍ ስለሆነ ይህን ልዕልና መራጩ ሕዝብም ሆነ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጎናጸፍ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የተለያዩ ሰዎች በፓርቲ ወይም በግል ተወዳድረው ሕዝቡ የኔ የሚለውን የመምረጥ እድል እንዲሰጠው ያስፈልጋል:: ይህ ደግሞ የሕገ-መንግሥቱን መለወጥ ወይም መሻሻል ይጠይቃል::
- በሕገ-መንግሥቱ ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት የሚበቃው ኢሕአዴግ የመረጠው ነው በሚል ስብስብ ትሕነግ በአምሳሉ የፈጠራቸው አራት ድርጅቶች ማለትም ትሕነግ/ሕወሓት ብአዴን/አዴፓ ኦሕዴድ/ኦዴፓ እና ደኢሕዴግ ብቻ ነው:: ሌሎች ቀርቶ አጋር ድርጅቶች የሚባሉት የሶማሌ፣ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻጉል እና የሐረሪ ክልል ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ኢትዮጵያን እንዲመሩ ዕድል አይሰጥም:: ይህም ሕገመንግሥቱ ለአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ከአራት ክልሎች ወይም ድርጅቶች ውጪ ያሉት መያዝ ቀርቶ እንዳያስቡ ተደርጎ የተቃኘ ነው:: ባጭሩ ለተወሰኑ ክልሎች የነጋሢነት መብት ሲሰጥ ሌሎቹን ተገዥ አድርጎ የፈረጀ ነው:: ይህ መታረም ያለበት ጉዳይ ነው:: የፖለቲካ ሥልጣን ብቃት ችሎታና የሕዝብ አመኔታ ያላቸው ሰዎች ተወዳድረው በሕዝብ ምርጫ ለሥልጣን በውክልና የሚይዙበት ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል:: ይህ እንዲሆን ደግሞ ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ወይም መለወጥ ግድ ይላል::
ይህ ጽሁፍ የተወሰደው ከ የአማራ ህልውና ለኢትዮፕያ አንድነት ድርጅት መግለጫ ነው።