ሰኔ 23,2011

ሰሞኑን በባህርዳርና በአዲስ አበባ የተከሰተው አደጋ እጅግ አሳዝኖናል፣ አስደንግጦናልም። በዚህ አደጋ በርካታ ወገኖቻችን መሞታቸውና መቁሰላቸው በመንግሥትና በነፃ ሚዲያ ተገልጿል። ባህርዳር በተፈጠረው ግጭት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ ሦስት ከፍተኛ የሥራ ባልደረቦቻቸውና የደህንነት ሀላፊው ጀኔራል አሳምነው ጽጌ መሞታቸው ተገልጿል። በአዲስ አበባው ግጭት የሞቱት ደግሞ፣ የጦር ሀይሎች ኢታማጆር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮነንና ጄኔራል ገዛኢ አበራ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ቁጥራቸው ያልተገለጸ በርካታ የአማራ ክልል የልዩ ሀይል፣ የሚሊሺያ አባላትና የፌደራል ወታደሮች መሞታቸውና መቁሰላቸው ታውቋል። ከዚህ ግጭት ጋር በተዛመደ በርካታ ዜጎች በባህርዳርና በአዲስ አበባ እየታሰሩ መሆናቸው ተዘግቧል። የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ድርጅቶች (CIVIC ORGANIZATIONS) ስብስብ በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ለሞቱና ለቆሰሉ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንመኛለን። በተጨማሪም በተፈጠረው ችግር በሀዘን የተጎዱትን የሟች ቤተሰቦች በማጽናናት፣ ሁኔታውንም በተረጋጋና በአብሮነት መንፈስ ለማጤን ማህበረሰባችን ለአሳየው አስተዋይነት ልባዊ አድናቆታችንን እንገልጻለን።

የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ለተረጋጋና ለበለጸገ ኢኮኖሚ፣ ለማይገረሰስ ልዑላዊነቱ መረጋገጥ ህዝባዊ ትግል ከጀመረ ረዥም ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ የተፈለገው ውጤት ላይ ለመድረስ መንገዱ እጅግ ውስብስብ ከመሆኑም በላይ በሰሞኑ ክስተት ግን ወደ ባሰ አዘቅት እንዳያሽቖለቁለው እንሰጋለን።

እንደሚታወቀው ከ1983 ወዲህ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ በአደገኝነቱ ወደር የሌለው በብሔርና በቋንቋ ክልል አስተዳደር  የተዋቀረው የፖሊቲካ ሥርዓት የአገራችንን ታሪክ፣ ቀጣይነትና የህዝባችንን አብሮነት ከባድ ፈተና ውስጥ ጥሎታል። በብሔርና በቋንቋ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያዳበራቸውን የባህል፣ የታሪክ፣ የሥነ ልቦና ትስስርና የአብሮነት የጋራ እሴቶችን የሚንድ፤ወደ እርስ በርስ ሁከትና ግጭቶች የሚወስድ ነው። እንዲሁም እንደሀገር የመኖራችንን ሕልውና የሚፈታተን የቁልቁለት መንገድ መሆኑ ታውቆ ከወዲሁ ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣቱ በፊት አስቸኳይና ደፋር የሆነ ሀገራዊ የመመካከሪያና የመደራደሪያ መድረክ የሚያስፍልግ ሆኖ አግኝተነዋል።

እንደ አለመታደል ሆነና በነዚያ በጀግኖች ወላጆቻችንና አያቶቻችን ተጋድሎ ለዓለም የነፃነት ወዳድ ሕዝቦች በተስፋና በተምሳሌነት እንዳልተጠራች ሁሉ ዛሬ ኢትዮጵያ ልጆቿ  በከፋ ድህነት፣ በመፈናቀልና በስደት በዓለም የብዙሃን መገናኛዎች የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነች። ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ቀናቶች በባህርዳርና በአዲስ አበባ ላይ በከፍተኛ የመንግሥት፣ የክልል፣ የሲቪልና የጦር ባለሥልጣኖች ላይ የደረሰው ግድያና የእስር ሁኔታ ሰላም ወዳዱን የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ አሳዝኖታል አሳስቦታልም።

እስከመቼ? ኢትዮጵያውያን በእንዲህ ዓይነቱ ያለመረጋጋትና የሰላም ማጣት፣ የእርስ በእርስ መጠፋፋት፣ስንታመስ እንኖራለን? የሚለው ወቅታዊ ጥያቄ አሁንም ምላሽ የሚፈልግ መሆኑ አይቀሬ ቢሆንም መፍትሄዎቻችንን በማስተዋል፣ የምንወስዳቸው እርምጃዎች በተረጋጋና በሰላማዊ መንገድ አንድነታችንን በማያናጋ ሁኔታ ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸዉ ። በመሆኑም የሚከተሉት ነጥቦች ላይ በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን።

  1. በግብታዊነት ስሜት ፣ በእልህ ፣ ቡድናዊ በሆነ አመለካከትና ባልተጨበጠ መረጃና በመላምታዊ እሳቤ(Theory) ላይ ብቻ በመመስረት መነሳሳት የሚያመጣው ውጤት የባሰ አለመረጋጋትና ሁከት እንጂ ሰላማችንንና አንድነታችንን አያስገኝልንም። በመሆኑም ቅንነትና እውነትን በጨበጠ ከአድርባይነት በፀዳ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብና አሰራር ላይ ብቻ መጓዝ አለብን ብለን እንመክራለን።
  2. በተለይም በአቋራጭ ወደስልጣን ለመንጠልጠል ወይም ያለመረጋጋትን በመጠቀም (ከየትኛውም ቡድን ይምጣ) አንድ ቡድን ለመጥቀም፣ ወይም ባላንጣን በእግረ መንገድ ለማጥፋት ተብሎ የሚወሰድ እርምጃን (ይዋል ይደር እንጂ መገለጡ ስለማይቀር – ኬኔዲን ማን ገደለው? ለምን?እንደተባለው ተዳፍኖ የማይቀር በመሆኑ) መቃወም ይኖርብናል።
  3. ለዚህ በባህርዳርና በአዲስ አበባ ለተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት መፈጠር አስተዋጽኦ ያደረጉ ቀጥተኛ ምክንያቶች፣ የተግባሩ ተዋንያኖችና አፈጻጻም ሂደትና ይዘት፣ ይህንንም ሁኔታ ተከትለው መንግስትና የጸጥታ ሀይሎች በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተሳታፊነት ወይም “በአሸባሪነት” ተጠርጣሪነት እየተወሰዱ ያሉ አርምጃዎች ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነቱን የማወቅ መብት አለው። ለዚህም በማንኛውም መመዘኛ ነጻ የሚባል አጣሪ አካል መቋቋም እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። ስለሆነም መንግሥት በእውነት ብቻ ላይ የተመሰረተና በገለልተኛ ወገን- የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ድርጅት (United Nations High Commission For Human Rights) ሊያረጋገጥው የሚችል መረጃና ማስረጃ ለህዝባችን በአስቸኳይ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት አበክረን እናሳስባለን።
  4. በተለይም በአማራው መንግሥታዊ ክልል ውስጥ የሚደረገው የርስ በርስ መወነጃጀልና መጠፋፋት ጎጅነቱ ያመዘነ በመሆኑ በአስቸኳይ ቆሞ ማህበረሰቡ ለጋራ ሰላሙና እድገቱ በተለመደዉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተከሰተውን ችግር እንዲፈታ እንማፀናለን።
  1. በነጻ አጣሪ አካል የማጣራቱ ጉዳይ እነደተጠበቀ ሆኖ፤ በተጨማሪም በመንግስት በኩል ለተለቀቁት እርስ በርስ የሚጋጩ ዘገባዎች በቂ ማብራርያ መሰጠት ይኖርበታል። ለተዓማኒነትም መለኪያ ይሆናል።
  2. ከሰሞኑ ግርግር ጋር በተያያዘ የፀጥታ ኃይሎች የሚያካሂዱት ዜጎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ዘመቻ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ በማስረጃ ጥፋተኝነታቸው በተረጋገጠ ተጠርጣሪዎች ላይ ያተኮረና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲከናወን ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥ በአፅንኦት እናሳስባለን።
  3. አንድም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወንጀሉ ሳይጣራ አይታሰርም ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተነገረ በኋላ መንግሥት እየወሰደ ያለው የጅምላ እሥር የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የጣሰና ትክክለኛ የሕግ አካሄድን (Due Process of the Law) ያላከበረ ስለሆነ ይህን ዓይነት እርምጃ ባስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን።
  4. የሲቪክና የተለያዩ የማህበረሰብ ስብስቦች ሕዝብ በሀገሩ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን፣ ሰላም፣ መግባባትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ሀገር ላይ ለመኖር አንዲችል ያግዙ ዘንድ መንግስት የሕግና የአፈጻጸም መሰናክሎችን በማስወገድ ተገቢውን ድጋፍ ያደርግላቸው ዘንድ እየጠየቅን፣ ይህም ችግር ላይ እየወደቀ ላለው የለውጥ ሂደት አይነተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ማስታወስ እንወዳለን።
  5. የፌደራል መንግስት ቀዳሚና ዋንኛው ሀላፊነቱ፣ የሀገሪቱን ድንበርና ሉአላዊነት ማስከበርና የዜጎችን መሰረታዊ ሰብአዊ መብት መጠበቅ መሆኑን እያስታወስን፣ በዚህ ጉዳይ ባለፈው አንድ አመት የለውጥ ሂደት ወስጥ ብቻ በሀገሪቱ ብዙዎች ህይወታቸውን ያጡበት፣ የአካል ጉዳተኞች የሆኑበትና በብዙ ሚሊዮን የሚቀጠሩ ዜጎች የሕይወት ዋስትና በማጣታቸው በሀገራቸው ወስጥ ስደተኛ የሆኑበትን ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው ሂደት አስቸኳይ የማስተካክያ እርምጃ በመውሰድ የፌደራል መንግስቱ ሀላፊነቱን ይወጣ ዘንድ እንጠይቃለን።

 

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ፍትህ የሰፈነባት፣ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ የህዝብ እኩልነት እውን የሆነባት አገር እንድትሆን የሁለችንንም ማስተዋል የተሞላበት፣ ትዕግሥትና ጥበብ የተዋሃደው፣ ስሜታችንን ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብን ማዕከል ያደረገ፣ ዛሬን ሳይሆነ ነገን ያሰበ፣ በሚያልፈው ሕይወታችን የማያልፍ ታሪክና ለትውልድ የሚተርፍ መስዋዕትነትን ከፍለን መተኪያ የሌላት ኢትዮጵያንና ሕዝቧን እንታደግ! የሚለው መልዕክታችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ በያላችሁበት ይድረሳችሁ።

 

ብሔረሰብንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እንቃወማለን።

ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር።

 

በዚህ መግለጫ የተሳተፉ የማህበረሰብ ድርጅቶች የስም ዝርዝር ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ናቸው::

  • የኢትዮጵያ፤የውይይትና፤መፍትሔ፤መድረክ
  • የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማዕከል
  • የኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ ኮሚቴ
  • ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት
  • ጋሻ ለኢትዮጵያ
  • ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
  • የቀድሞ የተባበሩት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ማህበር
  • የቀድሞ የጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሰራዊት ማህበር
  • የቀድሞ የኢትዮጵያ የአገር መከላከያና የፖሊስ ሰራዊት ማህበር
  • ኢትዮጵያዊነት (የዜግነት መብት ጥበቃ ካውንስል)
  • የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማዕከል
  • የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማዕከል በሰሜን ቨርጂንያ
  • የኢትዮጵያ ክፍላተሀገርሕብረት
  • ሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት
  • ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያዉያን ሴቶች ማህበር
2019-07-05T18:13:16+00:00