–ምርጫው ልማት ወይንም እልቂት ነው— አክሎግ ቢራራ (ዶር)
ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በፊት አይቶትና ሰምቶት የማያውቀውን የሰብአዊ መብት መከበር፤ በነጻ የመናገርና የመጻፍ፤ መንግሥትን የመተቸት፤ እንደልብ የመንቀሳቀስና የመደራጀት፤ የመሰብሰብ፤ ከአገር የመውጣትና የመግባት መብቶችን ተቀዳጅቷል። ችግሮችን በጋራና በሰላም የመፍታትና የኢትዮጵያን ጥልቀት ያለው የኋላ ቀርነትና የድህነት ሰቆቃ ለመቅረፍ እድሉ ከፍ ብሏል። ኢትዮጵያን ካስቀደምና ከዘውግ በላይ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብትና ደህንነት ለማሰብና ለመስራት ከቻልን፤
• ኢትዮጵያ በአስርት ዓመታት ረሃብን፤ ፍጹም ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለመቅረፍ ትችላለች፤
• ኢትዮጵያ ዩጎስላቭያን አትሆንም። ይህን ማድረግ ግን ቀላል አይሆንም፤ ብዙ አስመሳዮችና ጠባብ ብሄርተኞች የከበቡት መንግሥት ሆኗል።
መጀመሪያ የፖለቲካውን ችግር በጋራ፤ በቅንነትና በድፍረት ለመፈታት ፈቃደኛ መሆን አለብን። የመንግሥቱ መሪዎች ደፋር መሆን አለባቸው።
የኢትዮጵያን ረጅም፤ የሚያኮራና የጋራ ታሪክ ሂደት፤ የዘውግን ጠባብ ብሄርተኝነት አደጋነት፤ አድካሚነትና አፍራሽነት፤ የኢትዮጵያዊነትን የዜግነት መለያ ወይንም የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አስፈላጊነትና ወሳኝነት፤ ጦርነትን ወደ ጎን ትቶ ኋላ ቀርነትንና ድህነትን የመቅረፍና የማሸነፍ ወሳኝነትን ወዘተ እሴቶች በሚመለከት ብዙ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ይህች የብዙ ሽህዎች ዓመታት ታሪክ ያላት አገር በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገና ስለ አገር ግንባታ (Nation-building) ጥናት፤ ምርምርና ውይይት ታደርጋለች። ለማስታወስ፤ እኛ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን መናገር፤ መጻፍና መተቻቸት እንወዳለን። በጋራ እሴቶች መስማማት ግን አንችልም። “Quo Vadis Ethiopia (ኢትዮጵያ ወደ የት እየሄደች ነው?”) የሚለውን ጥያቄ ያልፈተሸ ምሁር ወይንም ስብስብ የለም። ይህ ባለፉት አምሳ ዓመታት ሲፈተሽ የቆየ ጥያቄ ሁሉም ምሁራን፤ ልሂቃን፤ የፖለቲካ ስብስቦች፤ መሪዎች የሚጋሩት መልስ አለማግኘቱ ይህች ታላቅ አገር አሁንም በራሷ ዜጎች እየተጎዳች መሆኑን ያሳያል። አገሩን የማያከብርና በማያሻማ ደረጃ የማይቀበል ዜጋ ወይንም ቡድን ሕዝብን ይወዳል፤ ለፍትህ ቆሟል ለማለት አይቻልም፤ የሚወደው ራሱንና የራሱን ዝና ነው። የሚያገለግለው የራሱንና የቡድኑን ጥቅም ነው።
የችግሩ መንስኤ ኢትዮጵያ ወይንም የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደሉም። ኢትዮጵያን እንደ ችግር የምናቀርባትና የምነወያይባት እኛው ነን። የቻይና ሕዝብ ቻይናን፤ የአሜሪካ ሕዝብ አሜሪካን፤ የራሽያ ሕዝብ ራሽያን፤ የኢራን ሕዝብ ኢራንን፤ የግብጽ ሕዝብ ግብጽን ወዘተ እንደ ችግር አያይም። የሰለጠነውና አገሩን ዘመናዊ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ የዓለም ሕዝብ፤ የፖለቲካውንና የፓርቲውን ልዩነት ከአገሩ ዘላቂነትና ብሄራዊ ጥቅም ይለያል። አገር እንደ ችግር አይታይም፤ ችግሩ የፖለቲካ ሥልጣን ፈላጊዎች ናቸው ። ዓለም ያደነቃትን አገር ኢትዮጵያን ዛሬም የምናዋርዳት፤ ሌላው ቀርቶ አሁንም በስሟ ፓርቲዎችንና ተቋማትን ለመሰየም የምንቸገረው፤ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት፤ የአገሪቱ አምባሳደሮች አይን ባወጣ ደረጃ የኢትዮጵያን ዘላቂ የንግድ፤ የመዋእለ ንዋይ ፈሰስ አስፈላጊነት ጥቅም፤ የሁሉም ዜጎቿ የመከበርና የመገልገል መብት፤ የአገራችን የመከበርና የዜግነት መለያችን መሆኑን የማስተጋባትን ግዴታቸውን ወደጎን ትተው ኤምባሲዎችን የራሳቸው ዘውግ አባላት መሰብሰቢያና መገልገያ ማድረጋቸው ምን ያህል ይህችን ታላቅ አገር ዝቅ እንዳደረግናት ያሳያሉ። የኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ የመላው ሕዝቧ እድገትና በሁለመናዋ ተሳታፊነት የህልውና ጥያቄ መሆኑን “ኢትዮጵያ ወደ የት እየሄደች ነው” በሚሉት ስብሰባዎች ስነወያይባቸው ቆይተናል።
ዛሬ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልጉት ተግባር እንጅ ዲስኲር አይደለም። ኢትዮጵያ ፍትሃዊና አስተማማኝ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመመስረት የምትችለው የሕግ የበላይነት፤ እውነተኛ እኩልነት፤ በዜግነት መብት የተመሰረተ፤ ብሄርና ቋንቋ ተኮሩን ሕገ መንግሥት የሚተካ ሌላ ሕዝብ ተወያይቶና ተስማምቶ የተቀበለው ሕገ መንግሥት ስኬታማ ሲሆን ነው። ችግሩ ሕገ መንግሥቱ አይደለም፤ አፈጻጸም ነው የሚለውን ብሂል አልቀበልም። በዜጎች መብት ላይ ያልተመሰረተ፤ ሕብረ-ብሄራዊነትን ያዳከመ ሕገ መንግሥት እንዴት አግባብ አለው ለማለት ይቻላል?
ያለውን የአንድ ፓርቲ ስርዓት ለማጠናከርና የጥቂቶችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ካልተፈለገ በስተቀር፤ በአሁኑ ወቅት፤ “ሕገ መንግሥቱ ይከበር፤ ምርጫ ለይስሙላ ይካሄድ” ማለቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ምክንያቱም፤ የብሄር ጥላቻው ስር እንደሰደደ ነው። ቅደመ ሁኔታዎች አልተመቻቹም። ከአዲስ አበባና ሌሎች ጥቂት ቦታዎች ውጭ ሰላምና እርጋታ፤ የሕግ የበላይነት፤ አስተማማኝ ኑሮ ወዘተ የለም። ከፍተኛ ሌቦችና ነፍሰ ገዳዮች በሃላፊነት ለፍርድ አልቀረቡም።
ለምሳሌ፤ ባለፈው ሳምንት፤ በ February 6, 2019 የመጀመሪያ ቀናት ብቻ በደምቢያ ወረዳ ጎንደር ጦርነት ተካሂዶ ቁጥራቸው ያልተረጋገጠ ዜጎች ህይወት አልፏል፤ ብዙ ኃብት ወድሟል። ዶቸ ቬላ እንዳታወቀው ከሆነ የችግሩ መነሻ በጭልጋ ወረዳ በሚኖሩ “የዐማራና የቅማንት” ወንድማማች ሕዝቦች መካከል በተከሰተ ልዩነት ነው። ይህን ልዩነት በተከታታይ እሳት እየጫሩ ያባባሱት ህወሓቶች መሆናቸው የሚከራክር አይመስለኝም። ህወሓት ሥልጣን ከመያዙ በፊት በዚህና በሌሎች የጎንደር አካባቢዎች የተጨፈጨፈው ሕዝብ ብዛት በቅጡ ባይታወቅም፤ በብዙ ሽህዎች ይገመታል። ዛሬም እንደ ትላንቱ፤ የህወሓቶች ዐላማ ጎንደርን ማውደምም ባይችሉ በዘረፉት ኃብትና በገዙት መሳሪያ ጎንደርንና ጎንደሬውን ማድቀቅና ማዳከም ነው። ይህ ሁኔታ ከቀጠለና ከተስፋፋ የሚካሄደው ጦርነት በመላው ዐማራ ሕዝብ ላይ እንደሚሆን መጠራጠር የለብንም። ችግሩ የጎንደሬው ብቻ አይደለም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝ ኑሮ ለመኖር የሚችለው ሰላምና እርጋታ ሲኖር፤ የስራ እድል በገፍ ሲፈጠር፤ የምርት ኃይሎች ሲስፋፉና አስተማማኝ፤ ጠናካራና ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ማህበረሰባዊ ኢኮኖሚ ሲፈጠር ነው። እምቅ ኃብት መኖሩ ብቻ እድልና ምርት ሊፈጥር አይችልም። ሰላም፤ እርጋታና ፍትህ፤ ሙሉ ተሳትፎ አስፈላጊ የሚሆኑት ለዚህ ነው። የርስ በርስ ግጭት ለእነዚህ አስፈላጊ ሁኔታዎች መሰናክል መሆኑን በተደጋጋሚ አሳስቤአለሁ። ጎንደር የጦር አውድማ ሆኖ መቆየቱን ማንም አይዘነጋውም። በቅማንት “ማንነትና የመሬት ይገባኛልነት” ስም ሲነግዱ የቆዩ ኃይሎች አሁንም ችግሩ እንዲፈታ አይፈልጉም። የውስጥ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ በራያና አዘቦም ጦርነት የሚጭሩ ኃይሎች አሉ። በአጠቃላይ ሲገመገም፤ ጨካኙ ህወሓት በጎንደር ዐማራ ሕዝብ ላይ የሚያካሂደው አዲስ “የውክልና ጦርነት (Proxy war) እና እልቂት በዘውግና በቋንቋ ልዩነት ላይ የተመሰረተው ሕገ መንግሥትና የአገዛዝ ስርዓት ውጤት ነው።
በጎንደር ከተማ ዙሪያ፤ በአዘዞ አካባቢ በየካቲት 1, 2011, የተካሄደውን ውንብድና ስመለከት ይህ በደለቡ ከብቶች ላይ የተካሄድ ጭካኔ የተካሄደው ድሃውን የዐማራ ሕዝብ በኢኮኖሚ ለመቅጣት መሆኑ አያከከራክርም። ከአምሳ በላይ የሚሆኑ ከብቶች ተቃጥለው መውደማቸው ብቻ አይደለም። ከዚህ ባሻገር የተከሰተው ሁኔታ፤ የጎንደር ሕዝብ ተቆርቋሪ የክልል ሆነ የፌደራል መንግሥት እንደሌለው ያሳያል። በአንድ በኩል የጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ መንግሥት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሪዎች በአዲስ አበባ እያስተናገደ ስለ ስደተኞች ሁኔታ ሲወያይ የጎንደር ዐማራ ሕዝብ ግን ለአደጋ ተጋልጦ ዘላቂ መፍትሄ አላገኘም። በሕዝብ ህይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ላይ የሚካሄድ ጥቃት የህልውና ጥያቄ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ላልፈው የማልችለው ሌላው ክስተት፤ የማንነትንና የድንበርን ጉዳይ በሚመለከት ጠ/ሚንስትሩ የሰየሟቸው የኮሚሽን አባላት መስፈርትና ቅይጥ (Composition) አከራካሪ ከመሆን ያለፈ መሆኑ ነው። ችግሩን የፈጠሩ ግለሰቦች የፈጠሩትን ችግር በማይፈታ ሁኔታ ተቋቁሟል፤ በተለይ የዐማራውን ሕዝብ በሚጎዳ ሁኔታ።
መስፈርቱ ምንድን ነው?
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን፤ ፍትህን፤ የሕግ የበላይነትን፤ እውነተኛ የዜጎች እኩልነትን፤ ዲሞክራሲን፤ ሚዛናዊና ዘላቂ ልማትን፤ ሰላም፤ እርቅና አብሮነትን፤ ብሄራዊ እርጋታን፤ የአካባቢ ጤንነትንና ተመሳሳይ እሴቶችን ተቋማዊ ለማድረግ ከተፈለገ ጠ/ሚንስትሩና ፓርላማው የሚያጸድቋቸው ኮሚሺኖች አባላት መስፈርቶች የማያሻሙና ያለፈውን የማይደግሙ መሆን ይኖርባቸዋል። ከእነዚህ መስፈርቶች መካከል የሚከተሉት አስፈላጊ ናቸው፤
• ከማንኛውም ወንጀል የጸዱ፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ያላጋጩ፤
• ታሪክን የማያዛቡ፤
• ለሁሉም ዜጎች እኩልነትና መብት የቆሙ፤
• የዘውግ ጥላቻ የሌላቸው፤
• በጠባብ ብሄርተኝነትና በትምክኽተኝነት ያልተበከሉ፤
• በሃቅኛነትና በህሊና ተገዥነት የሚያምኑ፤
• ለአጭር ጊዜ ጥቅም ህሊናቸውን የማይሸጡ፤
• ለሥልጣንና ለግል ዝና የማይሻሙ፤
• ሃላፊነት የሚሰማቸው፤
• በአርቆ አስተዋይነት እሴት የሚታወቁ።
በድህረ ገጾችና በማህበረሰባዊ መገናኛዎች የተሰራጨው ቅይጥ እንዳለ ከቀጠለ ግን የወልቃይት- ጥገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዘቦ ጉዳይ እንዳለቀለት እቆጥረዋለሁ። ግጭትና እልቂት ይከተላል። ህወሓት የፈለገውን ለመቀዳጀት በሚል ስሌት፤ የዐማራው ሕዝብ መሬቱን ይነጠቃል። በተለይ የሚጎዳ የጎንደር ዐማራ ሕዝብ ነው። ይህ ከሆነ ኢትዮጵያና ኢትዮጱያዊነትም አብረው ይጎዳሉ። ጎንደርን ማጥፋት ኢትዮጵያን እንደማጥፋት ነው!! የዐማራው ክልልና የፌደራሉ መንግሥት ይህን ሁኔታ ማክሸፍ ግዴታቸው ነው።
ወጣቱ ትውልድ ይህን ጉዳት ያውቀዋል፤ ይታገላል።
የዐማራው ሆነ ሌላው ወጣቱ ትውልድ በጉጉት የሚጠብቀውና የሚመኘው ግጭትን፤ ጥላቻን፤ ምዝበራን፤ አፈናን አይደለም። ይህንማ ለምዶታል፤ አልፈልግም ብሏል። የሚመኘውና የሚፈልገው ኑሮውን ማሻሻል ነው። ሆኖም፤ የስራ እድል ወይንም ኑሮን ለማሻሻል የራስን ኩባንያ የመመስረት እድል አሁንም ጠባብ ነው። መሬቱን ከተነጠቀ እድሉም ይጠባል። እድሜው ከአርባ ዓምስት ዓመት በታች የሆነው ወጣት ቢያንስ ሰባ በመቶ ይሆናል የሚለው ዘገባ ምስክር አያስፈልገውም። በያንዳንዱ ከተማና በመላው የአገሪቱ ክፍል ያለውን የወጣት ብዛት፤ በየጠለላው የሚተኛውን ወጣት ትውልድ የኑሮ ሁኔታ ብቻ ማየቱ ይበቃል። በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ 800,000 በላይ የሚገመተው ሕዝብ በጠለላ ይኖራል፤ ይራባል።
በዚህ ዓመት የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት ድርጅት (UNICEF) የኦክስፎርድ ዩንቨርስቲን የጥናትና ምርምር መሳሪያ፤ ሁሉን አቀፍ የድህነት መስፈርቶች መሰረት አድርጎ ባደረገው ዘገባ እድሚያቸው ከአስራ ስምንት በታች የሚገመተውን አርባ አንድ ሚሊየን ወጣት ኢትዮጵያዊያን ተመን መሰረት አድርጎ ከእነዚህ መካከል 36 ሚሊየን ወይንም ሰማንያ ስምንት በመቶ የሚገመቱት ድሃ ወይንም ፍጹም ድሃ መሆናቸውን አሳይቷል።
ይህ ምን ማለት ነው? ድህነት ወይንም ፍጹም ድህነት ማለት በቂ ምግብ፤ የጤና አገልግሎት፤ መጸዳጃ፤ ንጹህ ውሃ፤ አጥጋቢ መጠለያ፤ የትምህርት እድል፤ አስፈላጊ ዜናና መረጃ ወዘተ የማያገኙ በማህበረሰባዊ፤ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ለመሳተፍ እድል የሌላቸው ማለት ነው። በሰለጠነው ዓለም እነዚህ ፍላጎቶች መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ናቸው። ማንኛውም መንግሥት ባለው ዓቅም መሰረት እነዚህን ፍላጎቶች የማሟላት ግዴታ አለበት። አለያ ወጣቱ በመንግሥቱ ላይ ይነሳል!!
መንግሥት የዜጎችን፤ በተለይ የወጣቶችን የኢኮኖሚ መብት ካላስከበረና ፍላጎታቸውን ለማሟላት በቂ ጥረት ካላደረግ ግን በተከታታይ ትውልድ የሚከሰተው ተከታታይ ረሃብ፤ ድህነት፤ ስደት፤ ግጭት፤ የእርጋታና የሰላም አለመኖር ይሆናል። ይህ ሁኔታ ከቀጠለ ደሞ፤ ማንኛውም አገር ከድህነትና ከኋላ ቀርነት አሮንቃ ራሱን ነጻ ለማውጣት አይችልም። የኢትዮጵያ ዘገባ የሚያሳየው በክልሎች መካከል እጅግ የሚያስፈራ የሕጻናት የድህነት ልዩነት መኖሩን ጭምር ነው። በተለይ ተጎድተው የሚገኙት ክልሎች አፋር፤ አማራ፤ ደቡብና ኦሮምያ ናቸው። ሰላሳ አራት ሚሊየን የሚገመቱት ድሃ ህጻናት የሚኖሩት “በኦሮምያ፤ በአማራና በደቡብ ክልሎች” ነው።
ሁሉን አቀፍ የሆነ ድህነት ከተከሰተ ቆይቷል። “አስደናቂ ልማት ይታይባታል” በምትባለው ኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚገመተው የወጣቶች ወይንም የህጻናት ክፍል ፍጹም ድሃ ነው። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ለወጣቱ ትውልድ የተለየ ትኩረት፤ የተለየ ኢንቬስትመንት፤ የተለየ ፍትሃዊ የባጀትና የገቢ ስርጭት አለመደረጉን ነው። በጥቂቶች ለጥቂቶች ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ሲሰራ በሰማይ ጠቀሱ ሱቁ ዙሪያ የሚኖረው የድሃ ሕዝብ ብዛትና ጭንቀት ምን ይሆን? ብሎ የሚጠይቅ አዲስ ባለኃብትና ባለሥልጣን ብዙም አልታየም። ዛሬ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የለማኙ ብዛት እየጨመረ እንጅ እየቀነሰ አልሄደም። የኢኮኖሚው መዋቅር መለወጥ አለበት። ግዙፍ ኢንቬስትመንት (የመዋእለንዋይ ፈሰስ) መደረግ አለበት።
ከሁከት ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገር የህልውና ጥያቄ ነው።
ሰላም፤ እርጋታ፤ አብሮነት፤ ፍትህ፤ መልካም አስተዳደር ካለ ኢትዮጵያ ሌሎች አገሮች ከደረሱበት ልማት ለመድረስ ትችላለች የሚል እምነቴ አሁንም ጠንካራ ነው። ወጣቱ ትውልድ ግዙፍ ነው (The Youth Buldge) በሚባልበት ጊዜ፤ ይህ ትውልድ ራሱንና አገሩን ዘመናዊ ለማድረግ እምቅ ችሎታ አለው ማለት ነው። የመከከለኛ መደቡን ለመጨመርና ለማስፋት ይህ ትውልድ ወሳኝ ሚና አለው። አመቻችና ችሎታ ያለው መንግሥትና አመራር (Enabling and competent government leadership) ያስፈልጋል። ግጭት፤ ሁከትና ሌብነት ኃብት ያመክናል። መንግሥት ያለውን ባጀት ማህበረሰባዊ ጭንቀትን ለመፍታት፤ ሰላምንና እርጋታን ለማስጠበቅ ፈሰስ ካደረገው ህጻናትንና ሌሎችን ከድህነት ነጻ ለማውጣት፤ የአገሪቱን የምርት ኃይሎች ለማጠናከር ፈሰስ የሚያደርገው ባጀት ይባክናል ወይንም ይቀንሳል። የፖለቲካ ሥልጣንን እንደ ራሳቸው ርስትና ጉልት የሚያዩት ህወሓቶች፤ ኦነጎችና ሌሎች በመሳሪያ ኃይል ስልጣን መያዝ ያስፈልጋል የሚሉት ሁሉ ማሰብና ትኩረት መስጠት የሚኖርባቸው የሕጻናትና የሌላው ሕዝብ ኑሮ ካልተሻሻለ የፖለቲካው ስልጣን ግብግብ የትም እንደማያደርስ ነው። ይመስላል እንጅ፤ ሁከት፤ የርስ በርስ ግጭት፤ ማህበረሰባዊ ጭንቀት የማንንም ኑሮ አያሻሽልም። የሩዋንዳን፤ የቦስንያንና የሌሎችን በግጭት የተበከሉ አገሮችን የውድመት ምሳሌነት ማጥናቱ የሚረዳው ከልምዳቸው ለመማር ነው።
ምርጫችን ግጭት ሊሆን አይችልም። ምርጫችን ልማት ነው። የውጭ መንግሥታት፤ በተለይ የምእራቡ ዓለም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን፤ የመላው አፍሪካ ተስፋ አገር ናት የሚል ግንዛቤ ስላላቸው ዛሬ የሚካሄደውን ሰላማዊና መሰረታዊ ለውጥ የሚቃወሙ ኃይሎችን አይደግፉም። የውስጥ ጥናቶችና ምርምሮች፤ እውቅና ያላቸው የምእራብ አገሮች ምሁራንና ተመራማሪዎች፤ በተለይ አሜሪካኖች የሚሉት “ኢትዮጵያ ዩጎስላቭያ እንድትሆን አንፈልግም” ነው። የሚመኙት “ይህች ጥንታዊ አገር የደቡብ ኮሪያን ኢኮኖሚ አይነት ውጤት እንድትቀዳጅ ነው” የሚሉ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው። በአንድ በኩል በአሜሪካ፤ በሌላ በኩል በቻይና፤ በራሽያ፤ በኢራንና በሌልች ኃይሎች መካከል ያለው የኃይል፤ የንግድ፤ የዲፕሎማሲና የስትራተጂክ ፉክክር እየሰፋና ጥልቀት እየያዘ ስለሄደ ኢትዮጵያ ጠንካራ፤ ሃብታምና ዘመናዊ አገር እንድትሆን የሚፈልጉ ምእራባዊያን ብዙ ናቸው። ወሳኙ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ነው። ይህ ዘገባ የሚያሳየው ክስተት፤ የወደፊቷ ጠንካራ ኢትዮጵያ መላውን ከሳሃራ በታች የሚገኘውን ጥቁር ሕዝብ ሁሉ በሚያጠናክር ሁኔታ ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች ወደሚል ድምዳሜ እያመራ ነው።
አሜሪካኖች የቀይ ባህርና የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ለሌሎች መንግሥታት መገልገያ እንዳይሆኑ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ ብዙ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ለማጠናከር የምፈልገው ሃሳብ፤ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት የቻይናን፤ የራሽያን፤ የኢራንንና የሌሎችን መንግሥታት ስትራተጂክ ጥቅም ለማዳከምና የራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለማጠናከር ኢትዮጵያና ኤርትራ፤ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንዲጠናከሩ ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ። ይህን ስል ግን የማሳስበው ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም ለማስከበር የራሷን መርሆዎች መከተልና፤ በተለይ የራሷን የውጭ ግንኙነት ማጠናከር ይኖርባታል። ግጭት ግን ይህን እድል ያማክናል።
የምእራብ አገሮች፤ ለመገንጠል ወይንም የኢትዮጵያን መንግሥት ለማዳከም የሚሞክሩ ኃይሎችን፤ በተለይ መሪዎችን ክትትል እንደሚያደርጉባቸው የውስጥ አዋቂዎች ይጠቁማሉ። ኤርትራና ኢትዮጵያ የጀመሩት ወዳጅነት ደጋፊነት ያገኘበትም ምክንያት ከዚህ የአሜሪካኖች ስትራተጂክ ግንዛቤና ድምዳሜ ጋር አብሮ የተያያዘ መሆኑን እገምታለሁ። የጣሊያን መንግሥት በኤርትራና በኢትዮጵያ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን ጥንታዊ ግንኙነት ለማጠናከር በሚል ስሌት፤ የሃዲድ መንገድ ጥናት (Rail feasibility studies) ለማድረግ ቃል መግባቱ ጠቃሚና ወቅታዊ ነው።
ቻይናም በበኩሏ ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን የንግድና የኢንቬስትመንት ፍላጎቶች ለመቀጠል ውሳኔ ማድረጓን በግልጽ አስታውቃለⶭ። ኢትዮጵያ፤ የራሷን ጥቅም ለማስከበር ከቻይና የምትፈልገውን ከራሷ ጥቅም አንጻር ማየት አለባት። መጠንቀቅ ያለባት ግን፤ ለውጭ ምንዛሬ ሲባል የውጭ ኃይሎችን ማባበል አደገኛ መሆኑን ነው። የአረብ አገሮች ታላቁን የዓባይን ግድብ እንደማይደግፉ በተደጋጋሚ ጽሁፎቼ አሳይቻለሁ። እነሱ የሚፈልጉት ታላቁ ግድብ ትንሽ እንዲሆንና ለግብጽ የሚደርሳት ውሃ እንዳይቀንስ፤ ኢትዮጵያ ጠንካራና ራሱን የቻለ ኢኮኖሚ እንዳትፈጥር ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የአካባቢና የዓለም አቀፍ ሁኔት በጥንቃቄ መጠቀም አለባት። ይህ የአካባቢና የዓለም አቀፍ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ የውስጥ የፖለቲካ አጣብቂኝ በቀላሉ እንዳይፈታ የሚፈልጉ ኃይሎች ግትርነትና አጥፊነት ለተወሰነ ጊዜ የሚቀጥል ይመስለኛል። ውጣ ውረድም ቢኖር፤ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ በምንም አትፈርስም። የአሁኑን በያካባቢው በየቀኑ የሚከሰት ግጭትና ሁከት የፈጠሩት ኃይሎች ቀደም ሲል አስበውበት ነው። ህወሓትና አጋሮቹ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የፈጠሩትና ያስፋፉት የብሄር ጥላቻ፤ ልዩነትና የጥቅም ሰንሰለት በቀላሉ የሚፈታ ያልሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ብዙ ገበያተኞች ወይንም የፖለቲካ አትራፊ ሸማቾች ስለተፈጠሩ ነው። ህወሓቶችና ሌሎች የዘረፉት ኃብት ብቻ ይህን ጥላቻና ልዩነት፤ ቂም በቀልነትና የመገንጠል ዝንባሌ ሊያስቀጥል ይችላል።
ሌቦችና አጥፊዎች በሃላፊነት የሚጠይቁበት ወቅት አሁን ነው።
ደፋር አመራር አስፈላጊ መሆኑን አሳስባለሁ። ከፍተኛ ሌቦችንና ሃብት ያሸሹትን፤ ነፍሰ ገዳዮችንና ሽብርተኞችን ለሕግ ያለማቅረቡ ችግር ውጤቱ ግጭት ነው። ዘራፊዎችና ነፍሰ ገዳዮች በሃላፊነት ካልተጠየቁ የሕግ የበላይነት አይመለከተንም ወደሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ስለሚደርሱ ሰላምና እርጋታ እንዲፈጠር አይፈቅዱም። እኔ እስከማውቀው ድረስ ህወሓትና ኦነግ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ መብት የላቸውም። የተለየ መሳሪያ የመያዝ፤ ጦር የማንቀሳቀስ፤ ሽብርተኝነት የመጫር መብት አልተሰጣቸውም። ኦነግ እንደ ሌላው ውጭ እንደነበረ ኃይል ወደ አገር ቤት ገብቶ በሰላም እንዲንቀሳቀስና እንዲወዳደር ጥሪ ተደረገለት እንጅ ብዙ ሽህ የታጠቀ ወታደር እንዲያንቀሳቅስ፤ ባንኮችን እንዲዘርፍ ፈቃድና መብት አልተሰጠውም።
የደርግ መንግሥት ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የማስታውሰው ህወሓትና ሌሎች የታጠቁ ኃይሎች የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችን እየዘረፉ ማራቆታቸውን ነው። በተመሳሳይ፤ በ January 2019, ኦነግ የዐብይ መንግሥት የሰጠውን የነጻነት መብት ጥሶ ባንኮችን ዘረፈ፤ ንጹሃን እንዲሞቱና ብዙ ወገኖⶫችን ከቀያቸው እንዲባረሩ አደረገ። ይህ ለምን ሆነ፤ ለምን ዘላቂ ዓላማ? የሚለውን የሚጠይቁ ታዛቢዎች ያገኙት መልስ አንድ ነው። በጥቂት ወራቶች ለብዙ ዓመታት ያላገኘውን የፖለቲካ ስልጣን ለማግኘት የሚለው አንዱ መልስ ነው።
ይህ ከሆነ በህወሓትና በኦነግ መካከል ልዩነት የለም። ሁለቱም የቋንቋና የዘውግ ፌደራሊዝም ዘላቂ አላማው እያንዳንዱ ዘውግ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ ካልቻለ የመገንጠል መብቱን ስኬታማ የማድረግ መብቱ የተጠበቀ ይሆናል ማለት ነው። ዩጎስላቭያን መጥቀሱ አግባብ የሚኖረው ለዚህ ነው። ግን፤ ኢትዮጵያና ዩግስላቭያ የተለያየ የታሪክ ሂደት ያላቸው አገሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ዩጎስላቭያ አይደለችም። አለመሆኗን የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች አሉ። ኢትዮጵያ ነጻነቷን ያስከበረችው በሁሉም ዜጎቿ ተጋድሎና መስዋእት ነው። ይህ አብሮነት በብዙ ሁኔታዎች ተሰምሮበታል። ለምሳሌ፤ የዚህ ዓመት የጥምቀት በዓል በደመቀና አገር አቀፍ በሆነ ሁኔታ ተከብሯል። በበዓሉ ዙሪያ፤ የእስልምናና የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ህብረትና አብሮነት ያሳየው ኢትዮጵያ የጋራ አገር እንደሆነች፤ ሕዝቡ በኃይማኖት ልዩነት የማይከፋፈል መሆኑን ነው። ኢትዮጵያዊያንን የተለዩ ከሚያደርጓቸው እሴቶች መካከል በኃይማኖቶችና በዘውጎች መካከል ያለው የሚያኮራ ግንኙነት ነው። ይጋባሉ፤ ይጎራበታሉ፤ በክፉውም በደጉም ጊዜ ይገናኛሉ። አብረው አገራቸውን ከጠላት ይከላከላሉ።
በሶማልያና በኬንያ በተከታታይ የተካሄዱ የአልሸባብ እልቂቶች በኢትዮጵያ አልተከሰቱም። የኢትዮጵያ እስልምና ኢትዮጵያዊ ከሆነ ቆይቷል።ኢትዮጵያ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚነከባከቧት አገር ናት። ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ በኃይማኖቱም ሆነ በዘውጉ፤ በቋንቋው ሆነ በአመለካከቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚወክል ኢትዮጵያዊ መሪ ነው።
ማህበረሰባዊ ጭንቀትን ያባባሰው ምንድን ነው?
የጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ መልካም ምኞትና ጥረት፤ የአካባቢውና የዓለም ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፤ የአገሪቱን መሰረታዊ የስርዓት ችግር በሃቅ አቅርቦ መፍትሄውን የማቅረብ ደፋርነቱና ተከታታይነቱ ገና ስፋትና ጥልቀት አልያዘም። ለምሳሌ፤ አሁንም በቋንቋና በዘውግ የተመሰረተው የመለያያ ሕገ መንግሥት እንዳለ ነው። “የአፈጻጸም እንጅ የመርህ ችግር የለበትም” የሚሉ አሉ፤ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ጨምሮ። በኔ እምነት፤ ይህ ሕገ መንግሥት የችግሩ እምብርትና መሰረት ነው።
ነጻነት ከፍተኛ እሴት መሆኑ አያከራክርም። የማይካደው ክስተት፤ ቅድመ “ዐብይ” ፖለቲካ “ኮረንቲ ነው” ይሉ የነበሩና ድምጻቸውንና አቋማቸውን አሰምተው የማያውቁ ግለሰቦችና ስብስቦች ጭምር ከተደበቁበት ዓለም እየወጡ ተቆርቋሪነትና ወገንተኝነት ማሰማት ጀምረዋል። በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑት ጭምር። ግን ኃይላቸው የተበታተነ ሆኖ ይታያል። በተጨማሪ፤ ከዚህ በፊት ለማንነት ጥያቄ ትኩረት ያልሰጡ ኃይሎች “ነጻነት” አለን በሚል እምነት፤ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እኔም ክልል ይገባኛል ባዮች እየበዙ ሲሄዱ ይህ ሁኔታ የአማራውን፤ የኦሮሞውን፤ የደቡቡንና የሌላውን ክልል ሁሉ ይመለከተዋል። ይህ ከቀጠለ የክልሎች ብዛት ከአቅም በላይ ይሆናል፤ ኢትዮጵያ ዩጎስላቪያ የመሆን እድሏ ይጠነክራል። እኔ ቀረብ ብየ ስመራመረው፤ ጫፍ ላይ የደረሰውና በማህበረሰባዊ ሜድያ የሚለፈፈው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን አሁንም ዘውግ ተኮር ብሄርተኝነት፤ ባልካናይዜሽንነት (Balkanization)፤ ክልላዊነትና ራስን አገልጋይነት ነው። በጎንደር የሚካሄደው ግጭት የዚህ አካል ነው፤ ሆነ ተብሎ የሚካሄድ ሴራ!!
ዘውግ ተኮር አደረጃጀቱና ፉክክሩ፤ እኔም ክልል ያስፈልገኛል ባዩ እየጨመረ ሂዷል። አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ “ሃላፊነት የጎደለው ነጻነት እየተስፋፋ ሄዷል” በሚያስብል ደረጃ፤ መንደርተኛነት፤ ወገንተኛነት፤ ክልላዊነት ጥልቀትና ስፋት እየያዙ ነው። ይህን ችግር ብቻ ለማስታረቅና ለመፍታት የሚፈሰው ባጀት፤ ጉልበትና አቅም ግዙፍ ይሆናል። ለኢንቨስትመንት የሚውለው ባጀት እርጋታን ለመከባከብ ይውላል። የውጭ ምንዛሬ ይባክናል።
ላወቀበት ከነጻነት የበለጠ እሴት የለም። ሆኖም፤ ነጻነት ልክ እንደ እንቁላል በጥንቃቄ መያዝ አለበት። ካለተያዘ ተሰብሮ ሌላውን ይሰብራል። ጠፍቶ ሌላውን ያጠፋል። የማካይካደው ሃቅ፤ ከአንድ ዓመት በፊት ይሆናል ተብሎ ያልታሰበው ነጻነት ግን ከሃላፊነት ጋር ሊቆራኝ አልቻለም። እያንዳንዱ በየፊናው፤ የእኔ መብት ይከበር እንጅ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብት ይከበር ለማለት ካልደፈረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ወደ የባሰ አደጋ ሊሸጋገሩ ይችልላሉ። ያ ከሆነ የማንም መብት አይከበርም፤ መሳሪያ የያዘ አለቃ ይሆናል።
አንዳንድ በሕዝብ ፈቃድ፤ ፍላጎትና ምርጫ ሳይሆን፤ በትጥቅ ትግል ስልጣንን የመያዝና በጭካኔ የመግዛት ልምድ ያላቸው ክፍሎች አሁንም ከዚህ ኋላ ቀርና አጥፊ ልምዳቸው ራሳቸውን ነጻ አላወጡም። የነጻነትን ትርጉም ፋይዳ ቢስ ከማድረጋቸው ሌላ፤ ለእነዚህ ክፍሎች ሰርቶና አምርቶ፤ ተደጋግፎና አንዱ ለሌላው አስቦ መኖርና መብላት አዲስ ነገር ሆኖባቸዋል። የአገርን ኃብት መዝረፍና የዘረፉትን ግዙፍ ኃብት ለእልቂት፤ ለግጭት፤ ለርስ በርስ ጦርነት ማዋል መብታችን ነው የሚል ብሂል የሚከተሉ ኃይሎች ጥቂት አይደሉም። ከላይ እንዳቀርብኩት፤ ሁኔታውን ያባባሱትና የሚያባብሱት፤ ሌቦችና ነፍሰ ገዳዮች በሃላፊነት አለመከሳሰቸውና የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጭምር ናቸው። አሁንም ቢሆን የማያርፍ ጠላቶች፤ አገር ውስጥ ለሚገኙ አጥፊና አድካሚ ኃይሎች መሳሪያ በገፍ ይሸጣሉ። መሳርያ ለመግዛት የገንዘብ አቅም መኖር አለበት። ከእለት ጉርሱ ውጭ፤ ድሃው ሕዝብ መሳሪያ የመግዛት አቅምም፤ ፍላጎትም የለውም። የመግዛት ፍላጎትና አቅም ያለው፤ በአብዛኛው፤ ሳይሰራ ገንዘብ ያካበተው፤ ሰላማዊ ለውጥ የማይፈልገው ክፍል ነው።
ሰላምና እርጋታ ለፍትሃዊና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆናቸውን ምርምሮችና ጥናቶች በተደጋጋሚ አሳይተዋል። ለውጥን የማይፈልጉ ኃይሎች ግን የሚያስተጋቡት መልእክት “እኛ ስልጣኑን እስካልያዝን ድረስ” ሕግ አይከበርም። “ዐብይ የሚመራው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ጥሷል” የሚል ነው። ሕግ ካልተከበረ ሕገ-ወጥነት አግባብ አለው ማለታቸው ነው። ይህ ከሽፍታነት በምን ይለያል? ብየ ራሴን ስጠይቅ በምንም አይለይም የሚል መልስ አገኛለሁ። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው አማራጭ አንድ ነው። ማንኛውም ኃይል፤ ማንኛውም ዘውግ፤ ማንኛውም ድርጅት፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሕግን ማክበር አለበት።
መብት ሲባል፤ የትም ቦታ ይኑር የትም፤ የእያንዳንዱ ግለሰብ መብት ማለት መሆን መለመድ አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ ድርድር አያስፈልግም። አለያ፤ ፍትሃዊና ዘላቂ ልማትና ዲሞክራሲ አይቻልም።
የሕግ የበላይነትና የእያንዳንዱ መብት ካልተከበረ፤ ኢንቬስተሮች ኃብታቸውን ያሸሻሉ እንጅ፤ ምርትን ለማሳደግ የመዋእለ ንዋይ ፈሰስ አያደርጉም። የግልክፍሉና የግል ጥረት እንደጫጩ ይቆያሉ። የስራ እድል አይፋፋም። የምርት ኃይሎች በተፈለገው ደረጃ አያብቡም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮ የዋጋ ግሽፈት ይሰቃያል። ወጣቱ ትውልድ ወደ እምቢተኛነት ይሸጋገራል!! መሰደዱ ይቀጥላል!! በዘውግ መብት እየተመኻኘ፤ ዜጎች ከቀያቸው መባረራቸው ይቀጥላል።
ከዚህ ላይ ሳልጠቅሰው የማላልፈው የቅርብ ክስተት አለ። ይኼውም የዐማራ ብሄር አባላት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች፤ በብሄራቸው መለያ ብቻ ከሚማሩበት ተቋም በገፍ ሲደበደቡ፤ ሴቶቹ ሲዋረዱ፤ ሁለት ሽህ አምስት መቶ የሚሆኑት ከትምህርት ገበታቸው ሲባረሩና ወደ ባህር ዳር ሸሽተው ሲሄዱ የተሰጠው መልስ ያሳፍራል። የፌደራሉ መንግሥት ሁኔታው ተቀባይነት የለውም የሚል መግለጫና ማስጠንቀቂያ አልሰጠም። የዐማራው ክልል መንግሥት ተማሪዎቹ ተመለሰው እንዲሄዱ መከረ እንጅ እነሱ “ለህይወታቸው አስጊ ሁኔታ” መኖሩን ገልጸው በአማራው ክልል በሚገኙ ዩንቨርስቲዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያቀረቡትን አቤቱታ አልተቀበለውም። ለእነዚህ ተማሪዎች ተቆርቋሪው የበላይ አካል ማነው? የክልል ስርአቱ አደገኛና አግላይ፤ ኢሰሰብአዊ፤ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት መሆኑን በዚህ የቅርብ ምሳሌም ለማሳየት ይቻላል። ታዲያ ሕገ መንግሥቱ ችግር አይደለም የሚያስብለው መስፈርት የት ላይ ነው?
የለንደኑ አይነት ጉባኤ እንዳይደገም የማድረግ ግዴታ
የዘውግ ፖለቲካ ልሂቃን ራሳቸው ሁከትና ብጥብጥ እየፈጠሩ መንግሥት የለም ይላሉ!! በአብዛኛው መስፈርቶች ሳመዛዝናው፤ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ሰላምና እርጋታ አለ ባይባልም፤ ኢትዮጵያ “መንግሥት የላትም” የሚለው ብሂል ትክክል አይደለም። እርጋታና አስተማማኝ የሆነ የአገር ቀጣይነት ሁኔታ አለ ማለት አይደለም። እምቢ አልገዛም የሚሉ ኃይሎች፤ በተለይ ህወሃትና ኦነግ የሚያምኑበት ርእይቶና የሚከተሉት ዓላማ ስኬታማ ስላልሆነላቸው፤ ህወሓትና አጋሮቹ የፖለቲካ ሥልጣኑን ስለተነጠቁ፤ ኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጣን ሲይዝ የመሰረቱት ዘውግንና ቋንቋን መሰረት ያደረገው ህገመንግሥት ፈተና ገጥሞታል ይሉናል። ህወሓት መራሹ ቡድን ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የራሱን ሕገ መንግሥት ያከበረበት ወቅት ትዝ አይለኝም።
ህወሓቶና አጋሮቹ የፈጠሩትን ችግር ራሳቸው ሊፈቱት አይችሉም። ሊፈቱት ቢችሉ ኖሮ ብዙ እድል ነበራቸው። ምርጫ ዘጠና ሰባት የእድል ተምሳሌት ነው። እነ በረከት ሰምዖን ያደረጉት ግን የባሰ ድርጅታዊ ምዝበራ፤ የባሰ እልቂትና ስደት፤ የባሰ ተከታታይ ቀውስ እንዲከሰትና ኢትዮጵያ አምባገነናዊ አገዛዝ ስር እንዲሰድባት ነው። የለንደን ጉባኤ ስምምነት የዛሬው የስርዓት ችግር መነሻ ነው።
በሎንዶን ከተማ በ1991 ዓ.ም. የተካሄደው ጉባዔ አገር ወዳድ ግለሰቦችንና ህብረብሄር ፓርቲዎችን ያገለለ ነበር። ህወሓት በበላይነት፤ ኦነግና ሌሎች የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአጋርነት የመሰረቱት የመንግሥት አገዛዝ ስልትና የተስማሙበት ሕገ መንግሥት በዘውግ ልዩነትና በመለያየት መብትና አስፈላጊነት የተመሰረተ ነው። ክልል የመለያ ስያሜ እንጅ የአብሮነትና የህብረት ስያሜ አይደለም። ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ አይወክልም። ሌሎች የአፍሪካ አገሮች አደገኛና አፍራሽ መሆኑን አውቀው ያልተቀበሉት ሕገ መንግሥት መለወጥ አለበት የሚል እምነቴ አሁንም ጠንካራ ነው።
ከላይ እንዳሳሰብኩት፤ ጠ/ሚንስትሩ የሰየሙት የማንነነትና የድንበር ጉዳይ ኮሚሽን፤ በሃቀኛ መስፈርቶች ተመዛዝኖ፤ የክልል አስተዳደሮች፤ ባለሞያዎች፤ ምሁራን፤ አባቶች፤ እናቶችና ሌሎች ተቆርቋሪዎች በሕዝብ ውይይትና ግብዓት ያልተሰየሙበት ስለሆነ፤ በአብዛኛው ከጅምሩ አከራካሪና ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ ነው፤ እንደ ገና ቢታሰብበት ይሻላል የሚል ምክር እሰጣለሁ።
January 15, 2019, Foreign Policy “Don’t Let Ethiopia Become the Next Yugoslavia” በሚል አርእስት Florian Biber and Wondemagegn Tadesse Goshu ያቀረቡት ዘገባ እንዲህ ይላል። “Federations of ethnonational states can become explosive during moments of political liberalization, and Abiy must tread carefully to avoid a Balkan nightmare.” የችግሩ መንስኤ የለውጡ ሂደት ብቻ አይደለም። መሰረታዊ ለውጡን ፍጹም በሆነ ደረጃ አንቀበልም የሚሉ ኃይሎች መኖራቸው ጭምር ነው። የጠ/ሚንስትር ዐብይ መንግሥት ይህን ሁኔታ የማሻሻል ግዴታ አለበት። ለምሳሌ፤ ህወሓቶች በተደጋጋሚ “ሕገ መንግሥቱ ተጣሰ፤ የተገኘው የልማት ድል ሁሉ ተቀለበሰ” እያሉ ይጮሃሉ። የድብቅ ህወሓቶችና ኦነጎች ያሉበት ተቋም ሁሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። አብዛኛው የኢትዮያ ሕዝብ ሰላምና እርጋታ አለ እያለ ሲያስተጋባ፤ ህወሓቶችና ደጋፊዎቻቸው በአንድ ድምጽ “መንግሥት የለም፤ ሰላምና እርጋታ የለም፤ ነጻነት የለም” ይላሉ። የነሱ ደጋፊዎች የሆኑትን ማህበረሰባዊ ሚዲያዎች ይኼን ሃሰት እንዲያራምድ ጥረት ያደርጋሉ።
ለምሳሌ፤ በቅርቡ አገር ጎብኝተው የተመለሱ ግለስቦችና ቤተሰቦች ወደ ዐማራው ክልል፤ ወደ አዋሳና ሌሎች ቦታዎች ሂደው ሰላምና እርጋታ መኖሩን ይናገራሉ። በዚህ ዓመት የጥምቀት በዓል በጎንደርና በሌሎች ከተማዎች ሲከበር የፌደራሉ ኃይል ከሕዝቡ ጎን ቁሞ ሰላም አስከባሪ ከመሆን ሌላ አብሮ በዓሉን አክብሯል። የጎንደር ከተማ እንደዚህ ያለ ሰላምና እርጋታ አይታ አታውቅም የሚሉ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው። በ2015 የተካሄደውን የሚዘገንን እልቂት ማስታወስ ጥሩ ነው። የዛሬ ዓመት የመከላከያ ኃይሉ በያካባቢው ዜጎችን ያስር፤ ያቆስል፤ በጎንደር፤ በባህር ዳር፤ በደብረ ታቦርና ሌሎች ቦታዎች ይገድል ነበር። ህወሓቶች የሚፈልጉት ወንጀሉን፤ ግፉን፤ ግድያውን፤ ዘረፋውን አሁንም መቀጠል ነው። ላለፈው ግፍና በደል በሃላፊነት ያልተጠየቀ ኃይል (Immunity from being held accountable for past crimes and theft) የሚያስከትለው ሌላ ተከታታይ ወንጀል ነው። ማንም አይደፍረኝም ባይነት መቆም አለበት!!
ማንም አይደፍረኝም በሚል ድፍረት የሚሰማው ለፈፋና ጭካኔ መቀጠሉ ለኢትዮጵያዊያን ያሳፍራል እንጅ አያኮራም። ለውጥ መካሄዱ፤ ነጻነት መኖሩ ያኮራል እንጅ አያሳፍርም። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተከራከርኩት ሁሉ፤ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ሥልጣን ከያዙበት ወዲህ ኢትዮጵያ፤
1. ብዙ ሽህዎች የፖለቲካ እስረኞችን ፈታለች፤ አንድም የታሰረ ጋዜጠኛ የለም፤
2. ሁሉም “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” መሳሪያቸውን ፈተው ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ተደርጓል፤
3. ጠ/ሚንስትሩ በሚለያዩን እሴቶች ሳይሆን በምንጋራቸው የጋራ እሴቶች ዙሪያ እንድንነጋገርና እንድንወያይ ጠይቀዋል፤
4. የወደፊቷ ኢትዮጵያ በእርቅ፤ በሰላም፤ በፍቅር፤ በአብሮነት፤ በፍትህ፤ በእርጋታ፤ በተሳትፎ፤ በፍትሃዊ አገዛዝና በእውነተኛ ዲሞክራሲ እንድትመሰረት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ ተደርጓል፤
5. ከዚህ በፊት ባልተለመደ ደረጃ የጠ/ሚንስትሩ ካቢኔ ስርጭት ሴቶችን እንዲያስትፍ ተደርጓል፤
6. የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ በመሆኑ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የወንድማማች/እህትማማች ግንኙነት እንደ ገና እንዲታደስ ተደርጓል፤ የጋራ ግንኙነቱ ለሕዝቡ በሚጠቅም ሁኔታ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ይገመታል፤
7. በህወሓት መራሹ መንግሥት የተከሰተው አይን ያወጣ የዘውግ አድልዎ፤ ሌብነት፤ ሙስና፤ ኃብት ማሸሽ፤ ግፍና በደል መፍትሄ እንዲያገኝ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፤ ተቋማት ብሄራዊ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው፤
8. ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲጠናከር አገልግሎት እንዲሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው፤
9. የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ኤምባሲዎች ዋናው ተልኳቸው አገሪቱንና መላውን ዜጋ ማገልገል መሆኑ በማያሻማ ደረጃ ተገልጿል ወዘተ።
ይህም ሆኖ፤ የኢትዮጵያ 110 ሚሊየን የሚገመት ሕዝብ በያካባቢው በግጭት፤ በግድያ፤ በዝርፊያና በሌላ ህውከት ተበክሏል። ዘውግ ተኮር ግጭት ተስፋፍቷል። የፌደራሉ መንግሥት የሚመራበት መርሆና የክልል ፖለቲካ ልሂቃን የሚመሩበት መርህ ሊታረቅና ሊጣጣም አልቻለም። ምክንያቱም፤ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሆነ ተብሎ የተሰበከውና ወጣቱ ትውልድ እንዲማር የተደረገው ባህል የመለያየት፤ የጥላቻና ራስን የማገልገል ባህል ነው። የተወሰኑም ቢሆን፤ ለሰላም ቆመናል ብለው ቃል የገቡ ኃይሎች ሳይቀሩ፤ የተገኘውን ነጻነት ተጠቅመው ከዚህ በፊት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ቡድኖቻቸው የገቡትን ቃል ጥሰው እንዲታጠቁ፤ እንዲዘርፉ፤ እንዲገድሉ፤ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህገወጥነት እንድትጋለጥ፤ የርስ በርስ ጦርነት እንዲጀመርና አገሪቱ እንደ ዩጎስላቭያ እንድትበታተን ሞክረዋል ወይንም እየሞከሩ ነው።
“These conflicts in turn precipitate ill-conceived moves, including secession, which could have deadly consequences where violence has been the principal means of settling communal disputes.” የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልሂቃንና ቡድኖች የለመዱት ሥልጣንን በኃይል ብቻ መያዝ ስለሆነ አሁን የሚካሄዱት ግጭቶች የተለመዱ ናቸው።
የዚህን ማህበረሰባዊ ጉዳት ለማጤን፤ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ምን አይነት ኑሮ ለመኖር እንደሚፈልግና ኑሮው ስኬታማ ለማድረገ ምን አይነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ቅድመ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር መመራመር ያስፈልጋል። የልማት ጥናቶች እንዲህ ይላሉ። የመካከለኛውን መደብ ለማስፋት ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ሰላም፤ የአቅምና የስራ አፈጻጸም ጠንካራነት፤ ጥራት ያለው ትምህርት፤ጠንካራ ብሄራዊ ተቋማት፤ የዜጎች ተሳትፎ፤ የመፍጠርና የማምረት ሙሉ ተሳትፎ፤ የሕግ የበላይነት ወሳኝ ናቸው። በእነዚህ አገሮች ወጣቶችና ሴቶች ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ተሳትፎ አላቸው። በተለይ አስደናቂ እድገትና የመካለኛ መደብ እድገት የታየው በምስራቅ ኤዢያ ፓሲፊክ፤ በቻይናና በህንድ አገሮች ነው። ዝቅተኛ ተሳፎና እድገት የሚታየው ከሳሃራ በታች ባሉ አገሮች ነው።
በ 2000 ሃያ አምስት በመቶ የሚገመተው የዓለም ሕዝብ መካከለኛ መደብ ነበር። በ2019 በግምት 3.8 ቢሊየን ሕዝብ (የዓለም ሕዝብ ግማሽ) መካከለኛ መደብ ሆኗል። ይህ የሕዝብ አካል የኢኮኖሚ እድገት ሞተር ሆኗል ማለት ነው። ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች በግጭት፤ በኑሮ ውድነት፤ በስደት፤ በአካባቢ ውድመት፤ በአድልዎና በሙስና የተበከሉ ናቸው።
የኢትዮጵያን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ሁኔታ ቀረብ ብየ ስመራመረው ባለፉት አምሳ ዓመታት የተከተልነው የፖለቲካ መርሆ ግጭትና ንትርክ፤ እልቂትና የኃብት ውድመት ነው። እድገት አለ ቢባልም በዜጎች መካከል የተከሰተው የኑሮና የገቢ ልዩነት እጅግ በጣም አደገኛ ነው። የመካከለኛውን መደብ ስፋት፤ ጥልቀት፤ ማንሰራራትና መጨመር እድል አግዶታል። ሁኔታውን ያባባሱት ብዙ ሰው ሰራሽ ችግሮች አሉ።
ከእነዚህ መካከል፤ ኢትዮጵያ በቋንቋና በብሄር እንድትከፋፈልና ክልሎች የተለያዩ የእድገት እድሎች እንዲኖራቸው፤ ይህች ታሪካዊ አገር ልክ እንደ ቀድሞዋ ዩጎስላቭያ እንድትሆን መደረጉ አንዱና ዋናው ነው።
ለማታወስ ያህል፤ የኢትዮጵያ ቅርብ ወዳጅ አገር የነበረችው (በአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት) ዩጎስላቭያ፤ ችግሮቿን በብሄራዊ ውይይት፤ በሰላም፤ በፍቅር፤ በአብሮነትና በፍትህ ለመፍታት ባለመቻሏ ብዙ ህይወት ጠፍቷል፤ ብዙ ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ባክኗል፤ ታላቋ አገር፤ ቦስንያ-ሄርዘጎቪና፤ ክሮሽያ፤ ሜሶደንያ፤ ሞንቴኔግሮ፤ ሰርብያ፤ ስሎቫንያ፤ ኮሶቮና ራሷን እንድትችል የሆነችው ቮጀቮዲና ወደ ተባሉ ስምነት አገሮች ተከፋፈለች። ዛሬ የዓለም ሕዝብ “ሞንትኔግሮ” የምትባለው አገር የት ናት ቢባል አያውቃትም። ዩጎስላቭያ ግን ዘመናዊ ኢንዱስትሪና የመካከለኛ ገቢ ያሏት ዜጎቿ ከሶቭየት ሕብረት አገሮች የተሻለ ኑሮ የሚኖሩባት አገር ነበረች። የዘውግ ፖለቲካ፤ በቋንቋና በዘውግ የተመሰረተ አገር ሁሌም ግጭቶች ይገጥሙታል። ግጭቶቹ በሰላም ውይይት መፍትሄ ካላገኙ መገንጠል የመጨረሻው አማራጭ ይሆንና ራሳቸውን የማይችሉ ትንንሽ አገሮች ይፈጠራሉ። ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ይህን ሁኔታ ቢያስቡበት መልካም ነው።
በህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት ያደገውና የተወለደው ትውልድ (ማለትም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት ነው)፤ እንዲያምን የተገደደው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በራሱ ዘውግ፤ በራሱ የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲ፤ በራሱ ማንነትና በራሱ ጥቅም ነው። ለማነጻጸር፤ ከላይ የጠቅስኳቸው መካከለኛ መደባቸውን የልማት ሞተር ያደረጉት አገሮች ግን የሚያምኑት በአንድ አገርና በብሄራዊ ብሄርተኝነት ነው። ለምሳሌ፤ ቻይናን እንደ አገር፤ ቻይናዊነትን እንደ ዜግነት መለያ መቀበል ማለቴ ነው። ቬትናም፤ ኢንዶኔዢያ፤ የህንድ አገር፤ አሜሪካን ወዘተ የሚከተሉት ተመሳሳይ ሞዴል ነው። ከኢትዮጵያ ውጭ ከሳሃራ በታች የሚገኙ አገሮችም የሚከተሉት ተመሳሳይ መርህ ነው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየው አደገኛ የፖለቲካ ሂደት 9 ወይንም ከዘጠኝ በላይ የሆኑ የክልል መንግሥታት ስር እንዲሰዱ የሚገፉ የድብቅ ኃይሎች መኖራቸው ነው። “Similar to the former Yugoslavia, Ethiopia is a federal state with nine units organized along ethnic lines….The Tigray, Amhara and Oromo regions (around 80 percent of Ethiopia) have their names from their dominant ethnic groups.” ከመሰረቱና ከጽንሰ ሃሳቡ፤ ህወሓት፤ ብአዴን፤ ኦነግና ሌሎች የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተጠቀሙት ሕገ መንግሥት ህብረ-ብሄራዊነትን የሚጻረር፤ ዘውጋዊነትንና ልዩነትን የሚያጠናክር ነው። ህወሓት ብአዴንን ፈጥሮ የዓማራውን ሕዝብ ትወክላለህ ብሎ ፈረደበት። በረከት ሰምዖን በሙስና መከሰሱ መልካም ዜና ቢሆንም፤ ይህ ድርጅት እስካሁን ድረስ ራሱን ከህወሓቶች አላጸዳም።
በቅርቡ አስደናቂ መሰረታዊ ለውጥ እየተካሄድ ነው የሚለውን ብቀበልም፤ አሁንም ቢሆን ይህ ዘውጋዊነትና ጠባብ ብሄርተኝነት ስር እየሰደድ መሄዱ ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ አደገኛ ነው። “Ethiopia has been ruled for decades by the Ethiopian Peoples’ Revolutionary Democratic Front (EPRDF), a coalition of mostly ethno-regional political parties, dominated by the Socialist Tigray People’s Liberation Front (TPLF). Both combined nondemocratic traits with ethno-federalism.” ህወሓትም ሆነ ኢህአዴግ ብሄራዊና ዲሞክራሳዊ ፓርቲዎች አይደሉም። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተፈጠረውና ስር የሰደደው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባህል ኢትዮጵያዊነትን፤ አብሮነትን፤ ሰብእነትንና ሰብአዊ መብትን፤ ፍትህንና ዲሞክራሲን፤ የግል ክፍል ልማትን ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ የበከለና ያጠፋ ስርዓት ነው።
ዛሬ ህወሓትና መሰል ኃይሎች የሚያደርጉት ጥረት ህወሓትን ህወሓት መሰል በሆነ ሌላ ጨካኝ ፓርቲ መተካት ነው። በኔ ግምገማና እምነት፤ ዳግማዊ ህወሓት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት አጥፊ ነው፤ ሁሉም መረባረብ አለበት። ኢህአዴግም ቢሆን በብቸኛነት ኢትዮጵያን ዘመናዊ፤ ፍትሃዊና ዲሞክራሳዊ ለማድረግ አይችልም። ህብረ-ብሄራዊነት ማበብና ቦታውን መያዝ አለበት።
የፈለገውን ያህል ተሻሻለ ቢባልም፤ አንድ ፓርቲ ዲሞክራሳዊ አገዛዝና ሰፊ የመካከለኛ መደብ ሊፈጥር አይችልም። ውድድር መኖር አለበት። በተጨማሪ፤ “አብዮታዊ ዲሞክራሲና” ተወዳዳሪ ኢኰኖሚ፤ ‘ሊበራል ዲሞክራሲ” ተጻራሪ መርሆዎች ናቸው። ሊበራል ዲሞክራሲን ቢሆን መፈተሽና ከአገራችን ሁኔታ ጋር መጣጣም አለበት። መኮረጅ ይቁም።
ይህን ከዲሞክራሲ፤ ከፍትህ፤ ከእውነተኛ እኩልነት ወዘተ ጋር የሚጻረር የጥቂቶች ለጥቂቶች የፖለቲካ ኢኮኖሚ ባህል ከህብረተሰቡ ለማጽዳት ገና ብዙ መሰረታዊ፤ መዋቅራዊ፤ ባህላዊና የተቋማት ለውጥ ያስፈልጋል። ዘውግ ተኮር ፌደራሊዝም ቀስ በቀስ የፈጠረውና ያመረተው ዘጠኝ የተለያዩና የማይደጋገፉ የክልል መንግሥታትን ነው።
የወደፊቷ ኢትዮጵያ ዩጎስላቪያ እንዳትሆን ከተፈለገ ምን አይነት የመንግሥት፤ የፖለቲካ፤ የማህበረሰብና የኢኮኖሚ አገዛዝ (Governance) ያስፈልጋታል? ብየ ራሴን ስጠይቅ አሁን ያለው ዘውግ ተኮር ፌደራሊዝም አለመሆኑን በማያሻማ ደረጃ እጠቁማለሁ። ይህ ሃቅ ብዙ ትንተና፤ ጥናት፤ ውይይትና ጉባኤ አያስፈልገውም። ኢትዮጵያ የዩጎስላቭያ እድል እንዳይገጥማት ከተፈለገ መሰረታዊና ስር ነቀል የሆነ ዲሞክራሳዊ ለውጥ መቀጠል አለበት።
ሕገ መንግሥቱ በአስቸኳይ መለወጥ አለበት። የሕገ መንግሥቱ መሰረት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁለመናዊ መብት የሚከበርበት መሆን አለበት። በአንድ አገር የተለያዩ “መንግሥታት” ስልጣን ይዘው ሊቆዩ አይችሉም። ይህ ከሆነ ሌሎች አገሮች ከደረሱበት የልማት ደረጃ ለመድረስ አይቻልም። “Without careful management of the delicate transition, Ethiopia risks a dangerous fragmentation along ethnic lines.” የነገዋ ዩጎስላቭያ የመሆን አደጋ ይደርስባታል የሚለውን አልቀበልም። እንጠንቀቅ ግን እላለሁ።
አደጋውን ለመፍጠር የሚፈልጉን ኃይሎች በማባበል ብቻ ለመቋቋም እንደማይቻል አምናለሁ። ለዚህ አደጋ ዋናው ምክንያት “ተገንጣይ” ኃይሎች ብቻ አይደሉም። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና “ተፎካካሪ” ፓርቲዎች የሚከተሏቸው ፍኖተ ካርታዎች (Road maps) ሊጣጣሙ አለመቻላቸው ጭምር ነው። ለምሳሌ፤ በቅርቡ ስማቸውን የቀየሩት ብአዴን ወደ ዐማራ ዲሞክራቲክ ፓርቲ፤ ኦህዴድ ወደ ኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ስማቸውን መቀየራቸው እመርታዊ ለውጥ ሆኖ አላገኘሁትም። አሁንም የያዙት በዘውግ የሚለዩበትን ስም እንጅ በኢትዮጵያዊነታቸው የቆሙበትን እመርታዊ ለውጥ አያሳይም። ሁለቱ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን መለያ ስማቸው ይዘው ህብረብሄራዊ ፓርቲ የማይሆኑበት ምን ምክንያት አላቸው?
በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት እናምናለን ያሉትንና የሚሉትን እየተቀበልኩ፤ ሁለቱ ፓርቲዎች ውህደት ለመፍጠር የማይችሉበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ አቀርብላቸዋለሁ። ይህ ካልሆነ አንዱ ሌላውን ለማጥቃት የሚደረገው የፖለቲካ ትግል ይቀጥላል፤ ህወሓትን አስወግዶ ሌላ ህወሓት መተካት ማለት ነው። በዐማራው ዲሞክራሳዊ ፓርቲና በዖሮሞው ዲሞክራሳዊ ፓርቲ መካከል ያለው ግንኙነት እየጠነከረና ህብረ ብሄራዊ እየሆነ ካልሄደ ህወሓት ያለውን ልዩነት ይጠቀምበታል። ከፋፍለህ ግዛውና መዝብረው ይቀጥላል።
በቲቶ ዘመን ዩጎስላቭያ “የክልሎቿ ሕዝቦች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ” አድርጋ ነበር። በተመሳሳይ፤ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና የነጻነት ጮራ ስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው የማድረጋቸውን ቅንነት የዘውግ ልሂቃንና ፓርቲዎች የራሳቸውን ጠባብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም እያስፋፉበት ይገኛሉ። አድር ባይብነት ጎልቶ ይታያል። እያንዳንዱ የዘውግ ፓርቲ የራሱን ክልል መሬትና ሕዝብ ለራሱ ጥቅም ብቻ እንዲወክል በማድረግ ላይ ይገኛል። ህወሓት የትግራይን ክልል “መንግሥት” የሌቦችና የጨካኞች ምሽግ ሲያደርግ፤ በተመሳሳይም ባይሆን በመጠኑ፤ ኦነግም እድሉን ተጠቅሞ አስራ ሰባት የሚሆኑ የባንክ ቅርንጫፎችን ዘርፏል ወይንም እንዲዘረፉ አድርጓል። በንጹህ ሕዝብ ላይ እልቂት አካሂዷል ወይንም እንዲካሄድ አመቻችቷል።
የዩጎስላቭያን ምሳሌ በመጥቀስ ተመራማሪዎቹ እንዲህ ይላሉ። “Thus, nationalists could easily capture the republics (እኛ ክልል የምንላቸውን ማለት ነው), leading to secession, ethnic cleansing and wars). ቦዝንያና ሌሎች የዩጎስላቭያ ክፍለ ሃገሮች እንደሆነው ማለት ነው። ለምርኮ የሚዳረጉት ክልሎች ብቻ አይሆኑም፤ ኢትዮጵያም ናት!!
ተከታታይ የርስ በርስ ግጭት የሚያስከትለው ጠንቅ ምንድን ነው?
የመዋእለንዋይ ፈሰስ መቀነስ፤ የኑሮ ውድነት፤ የጥቁር ገበያ መስፋፋት፤ የመሳሪያ ሸቀጥ መስፋፋት፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ የኃብት ሽሽት፤ የስራ እድል መጥፋት ወይንም መቀነስ፤ ሕዝቡ በፌደራል መንግሥቱ ላይ ያለው እምነት መቀነስ፤ ሰላምና እርጋታ እየተበከለ መሄድና ሌሎች አስጊ ሁኔታዎች መከሰታቸው ሊካድ አይችልም።
እንዚህ ሁኔታዎች አሉ ቢባልም ኢትዮጵያ “ዩጎስላቭያ” አይደለችም፤ አትሆንም የምልበትን ምክንያት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፤
1. የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮና ተቻችሎ የመኖር ባህሉ ተከታታይና ጠንካራ ነው፤ ተጋብቷል፤ ተዋልዷል፤ ተዛምዷል፤
2. የኢትዮጵያ ሕዝብ የውጭ ጠላቶቹን በጋራ ሆኖ የመቋቋም ልምድና ባህል አለው፤ ኋላ ቀርነትንና ድህነትንም አብሮ ለመቅረፍ እድሉ ከፍተኛ ነው፤
3. ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራችና መዲና ናት፤ ይህ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚኮራ ነው፤
4. አብዛኛው ወጣት ትውልድ የህወሓትንና የአጋሮቹን ግፍና በደል፤ አድሏዊነት፤ ጠባብ ዘረኛነት፤ መዝባሪነት ተቃዋሚ ነው፤ የዐብይን ለውጥ አድናቂና ደጋፊ ነው፤
5. የዐማራውና የኦሮሞው ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች፤ የደቡብ ሕዝብ ፓርቲ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነት፤ ነጻነትና የሕዝቧን አብሮነት በማያሻማ ደረጃ ደጋፊዎች ናቸው፤
6. የዐብይ መንግሥት መሰረታዊ የሆኑትን ብሄራዊ ተቋማት (የምርጫ ቦርድ፤ የፍትህ፤ የመከላከያ፤ የደህንነትና ሌሎችን) ተቋማት በማሻሻልና በማጠናከር ላይ ነው፤
7. የዓለም ሕብረተሰብ፤ በተለይ የአሜሪካ፤ የአውሮፓ፤ የጃፓን፤ የቻይናና ሌሎች መንግሥታት የኢትዮጵያን መንግሥትና መሰረታዊ ለውጥ እየደገፉ መታየታቸው፤
8. ዓለም ባንክ፤ አይ ኤም ኤፍና ሌሎች ግዙፍ የልማትና የገንዘብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የወደፊት ልማት ላይ እምነት ያላቸው መሆኑን በተደጋጋሚ መጠቆማቸው፤ ዓለም ባንክ ግዙፍ ድጋፍ መስጠቱ፤
9. አብዛኛው የዲያስፖራ አካል የዐብይን መንግሥት ደጋፊ መሆኑ፤
10. የዐብይ መንግሥት ፍትሃዊ ልማትና ዘላቂ እድገት እንዲመሰረት ማስተጋባቱና ለኢትዮጵያ ዘላቂነትና ለኢትዮጵያዊነት ተቀዳሚነት ያለውን ቆራጥነት በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ ማስታወቁ ይገኙበታል።
ይህ ለልማት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፤ የህወሓትና የኦነግ አክራሪነት፤ የማህበረሰባዊ ሜድያ መረን የለቀቀ አጥፊነትና የብሄራዊ ተቋማት ደካማነት የሚካሄደው መሰረታዊ ለውጥ ረዢም ጊዜ የሚጠይቅና በብልሃትና በጥበብ መመራት እንዳለበት ያሳያል።
የኢትዮጵያ “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ከመቸውም በበለጠ ደረጃ ወደ ውህደት መሸጋገር ያስፈልጋቸዋል።
በተመሳሳይ፤ ኢህአዴግም በዘውግ የተመሰረተውን የፖለቲካ ባህሉን ለመቀየር መድፈር አለበት። ለምሳሌ፤ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከዱሮው ስርዓት የወረሱትን አደረጃጀት ለውጠው ወደ ሕብረብሄራዊ ፓርቲነት የሚቀየሩበት ወቅት ዛሬ እንጅ ኢትዮጵያ የቀድሞዋን ዩጎስላቭያ ከሆነች በኋላ አይደለም። ኢትዮጵያ ሶሪያን እንድትሆንም መፍቀድ የለባቸውም፤ ሕብረብሄራዊነት ለዚህ ይጠቅማል (It is a mitigating factor). “Ethnic parties usually maximize their support not by moderation but by polarization.”
የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በዘውግ ተደራጅተውና ተሰይመው ሌሎችን ለምን “ጠባብ ብሄርተኛና ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት፤ ጸረ-ዲሞክራሲ ትሆናላችሁ” ሊሉ አይችሉም፤ የሞራል ብቃት አይኖራቸውም።
የዐብይ መንግሥት በጥናትና በምርምር ተደግፎ፤ ሕዝብን አሳትፎ በአስቸኳይ ሕገ መንግሥቱን መለወጥ አለበት።
የኔ ምኞትና ተስፋ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ዘውጋዊ ጥላቻ፤ አድካሚና ሃብትን፤ ጉልበትን፤ እውቀትን፤ ህይወትን፤ የሚያመክን ግጭት ተላቃ ሌሎች ከደረሱበት የመካከለኛ መደብ ደረጃ እንድትደርስ ነው። የኔ ምኞትና ተስፋ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዜግነቱን መብት ተጠቅሞ፤ በማንኛውም ኢትዮጵያ ለመኖር፤ ኃብት ለማካበት፤ ለመምረጥና ለመመረጥ የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው።
ችግሯ አገሪቱ ወይንም ሕዝቡ አይደለም። መሰረታዊ ችግራችን፤ ጠባብ ብሄርተኝነት፤ ትምክኸተኛነት፤ የስልጣን ፉክክርና የኢኮኖሚ ስግብግብነት ነው። እነዚህ ችግሮች በማባበል አይፈቱም፤ የሚፈታቸው የሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ስኬታማ ሲሆን ነው። ሕዝቡ የኃብቱ ባለቤት ሲሆን ነው።
Revised slightly from a version of January 23, 2019 published in Ethiopia.
አ/ቢ February 9, 2019